ኒው አፍሪካን መፅሄት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ጨምሮ 7 ኢትዮጵያውያን በ100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ዝርዝር ውስጥ ማካተቱ ተገለጸ

ኒው አፍሪካን መፅሄት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ 7 ኢትዮጵያውያን የ2018 100 ተፅእኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ዝርዝር ውስጥ አካቷቸዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረመድህን እና የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፍሬህይወት ታምሩ ይገኙበታል።

ተፅዕኖ ፈጣሪ ተብለው የተዘረዘሩት አፍሪካውያኑ በ2018 በአህጉሪቱ የተለመዱ ትርክቶችን መቀየር የቻሉ፣ ከአህጉሪቱ ውጪ ባሉ ዳያስፖራ አፍሪካውያን ዘንድ አወንታዊ ለውጥ ማምጣት የቻሉ እና በቀጣይ በጎን ስራ ይሰራሉ ተብሎ የሚታመንባቸው መሆናቸውን ነው መፅሄቱ የጠቆመው።

ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና ግብፅ በመቀጠል በርካታ ሰዎችን በዝርዝሩ ውስጥ ማካተት ችላለች።

መፅሄቱ እንዳስታወቀው በታሪኩ ለመጀመሪ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች በእኩል ቁጥር የተካተቱበት ተፅዕኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ዝርዝርን አውጥቷል።

መፅሄቱ በ2018 የፈረንጆቹ ዓመት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ለወጥን ይዘው የመጡ ያላቸውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመንግስታቸው ካቢኔ ውስጥ የፆታ ተዋፅኦን በእኩል ማድረጋቸው እና የመፅሄቱ ተፅእኖ ፈጣሪ አፍሪካውያን ቁጥር በእኩል የፆታ መጠን መውጣቱ በአጋጣሚ የሆነ ስኬት መሆኑን ነው ያነሳው።(ኤፍቢሲ)