የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) አመራሮች ወደ ሀገራቸው ገቡ

የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ከፍተኛ አመራሮች ወደ ሀገራቸው ገብተዋል።

አመራሮቹ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ኡመር፣ የሶህዴፓ ሊቀ መንብር አቶ አህመድ ሺዴ፣ የተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ሰራዊት አባላት ከሁለት ሳምንት በፊት ትጥቅ በመፍታት ከአስመራ ወደ ጅግጅጋ መግባታቸው ይታወሳል።

ከአንድ ወር በፊት በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ በማምራት ከቡድኑ ጋር ባደረገው ድርድር ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።

በዚህም ለረጅም አመታት የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየው ግንባሩ፥ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ስምምነት ላይ መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልፀው ነበር።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ መቀመጫቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ ኃይሎች የትጥቅ ትግል በማቆም ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። (ኤ.ፍ.ቢ.ሲ)