ለዘላቂ ሠላም መስፈን አገር ተረካቢ ህጻናትን ስለ ሠላም ማስተማር እንደሚገባ የሠላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን አገር ተረካቢ ህጻናትን ስለ ሠላም መስበክና ማስተማር የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ።

በአገሪቱ ሠላም ለማስፈን የሚደረገውን አገራዊ እንቅስቃሴ የሚደግፍና በጉዳዩ ላይ የሚመክር የህጻናት ፓርላማዎች አገራዊ የሠላም ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የሠላም መናጋት በአገር ህልውናና ሁለንተናዊ እድገት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።

የህጻናትን ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ከሚጥሱ፣ በትምህርታቸው፣ በጤናቸው፣ በስነ-ልቦናና አጠቃላይ እድገታቸው እንዲሁም ደህንነታቸውን ስጋት ላይ ከሚጥሉና መጻኢ ተስፋቸውን ከሚያጨልሙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች እንዲጠበቁ ማድረግም ግድ ይላል ነው ያሉት።

ለዚህም የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢና አለኝታ የሆኑ ህጻናት ስለ ሠላም ፋይዳ እንዲረዱና የሠላሙ አንድ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል።

ሠላምን በማስጠበቅና ለእሱም ዋስትና እንዲሰጡ ማድረግ ደግሞ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሃላፊነት መሆን እንዳለበት ነው ሚኒስትሯ ያስገነዘቡት።

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለምጸጋይ አስፋው በበኩላቸው የሠላም እጦት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጎጂ እንደሚያደርግ ቢታመንም የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎችና የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑት ህጻናትና ሴቶች ናቸው ብለዋል።

ስለሆነም አገር ተረክበው ወደላቀ የስኬት ማማ የሚያደርሱ ህጻናት በዓለምና በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተጎናጸፏቸውን መብቶች ‘ማረጋገጥ ይገባል’ ብለዋል።

ሠላም የእድገትና ብልጽግና መሰረት በመሆኑ ሁሉም ህጻናትና የህጻናት ፓርላማዎች እንደ ዜጋ በየአካባቢያቸው ሠላም ለማስፈኑ ሂደት ትኩረት እንዲሰጡና ተሳትፏቸውን እንዲያጎለብቱ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የህጻናት ፓርላማ ተወካዮችም ህጻናት በየአካባቢያቸው የሠላምን ፋይዳ እንዲገነዘቡ በማድረግና የአገራቸውን አንድነት በማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

መሰል የሠላም ኮንፈረንሶች የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትን አመለካከት የሚገነባና በመልካም ምግባር የሚቀርጹ በመሆናቸው ቀጣይነት እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

“ሰላም ለህጻናት” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው አገራዊ የሠላም ኮንፈረንስ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ከ1 ሺህ 200 በላይ የህጻናት ፓርላማዎች አመራሮችና አባላት ተሳትፈውበታል። (ኢዜአ)