በጉራጌ ዞን መስቃንና ማረቆ ወረዳዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ በቡታጅራ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን መስቃንና ማረቆ ወረዳዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ በቡታጅራ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል ።  

በመስከረም 3፤2011 ዓ.ም በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች መካከል በተከሰተው ግጭት መጠነኛ ጉዳት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል ።

ግጭቱን ተከትሎ ከኦሮሚያና ደቡብ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች የተውጣጡ የሀገር ሽምግሌዎች የእርቅ ሂደት ጀምረው እርቀ ሰላም ለማውረድ ቀነ ቀጠሮ በያዙበት ሁኔታ በህዳር ወር ግጭቱ ዳግም ማገርሸቱም ተገልጿል ፡፡

በመሆኑም ግጭቱ እንዲባባስና ከጀርባ ሆነው ሁኔታዎችን ሲያቀነባብሩ የነበሩ ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡና የህግ የበላይንት መከበር አለበት በማለት የመስቃን ወረዳና የቡታጅራ ከተማ ነዋሪዎች ህዝባዊ ሰልፍ አድርገዋል፡፡  

ግጭቱን በመሸሽ በቡታጂራ ከተማ ተጠልለው በሚገኙት  ዜጎች ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትም ለህግ ማቅረብ እንደሚገባ የሚገልጽና ኢ-ሰብዓዊ  ድርጊቱንም የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ ነው ያካሄዱት፡፡

በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች የሚገኙ ዜጎች ለዘመናት ተዋልደው፣ ተዋደውና ተከባብረው መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን በቅርብ ጊዜያት በጎረቤታሞች መካከል ግጭት በመቀስቀስ የተሳተፉ ግለሰቦች እንዲጠየቁና መንግስትም አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የሰለፉ ተሳታፊዎችና አስተባባሪዎች ጠይቀዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ ግጭቱን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋምና የፌዴራል መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ እንዲያወያይ በሰልፉ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ ከወረዳ አንስቶ እስከ ክልል ባሉ አመራሮች አሁን ባለው የውጥ ሂደት  ተለይተው ህዝቡ ወደ ቀደመው ህይወቱ ተመልሶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞርም የሰልፉ አስተባባሪዎች ጠይቀዋል፡፡

በግጭቱ ህገ ወጥ መሣሪያ የታጠቁ ግለሰቦች በመሠማራት በመስቃን ወረዳ  ነዋሪዎች ላይ ጥቃት እንደደሰ እና የዜጎች ህይወት እንደጠፋ እንዲሁም በማሳ ላይ የሚገኝ ምርት መውደሙንም አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡