በሶማሌ ክልል አሁን የመጣውን ሰላም ለማስጠበቅ ህዝቡ ከአዲሱ አመራር ጋር በአንድነት ሊሠራ ይገባል– የደገሃቡር ከተማ ነዋሪዎች

በሶማሌ ክልል አሁን የመጣውን ሰላም ለማስጠበቅ ህዝቡ ከአዲሱ አመራር ጋር በአንድነት ሊሠራ እንደሚገባ በክልሉ የደገሃቡር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

የክልሉ የሰላም ሁኔታ ወደ ቀድሞ አቋም መመለሱን የተናገሩት ነዋሪዎቹ ከዚህ በፊት ተነፍጎ የነበረውን የልማት ጥያቄዎችን ማንሳት፣ ሃሳብን በነፃነት መግለጽ እና መቃወምን በአሁኑ አመራር ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

ለዋልታ አስተያየታቸውን የሠጡት የከተማዋ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በነበሩ አመራሮች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይፈጸምባቸው እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ ግን በሰላም ወጥተው መግባት እንደቻሉም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም አሁን የታየውን  ለውጥ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሠሩ እና የክልሉ ህዝብም ከአመራር ጎን ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡