በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘውና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ ወንድማቸው አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ የአለም ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አለም ፍጹም ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ለ2ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

በሰኔ16 የቦንብ ፍንዳታ የተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌና ሌሎች ተጠርጣሪዎቹም በዛሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበዋል።

ፍርድ ቤቱ በተለያዩ መዝገቦች ለመርማሪ ፖሊስ በተሠጠውን የጊዜ ገደብ መሠረት  በተናጠል የሠራውን ምርመራ ለችሎቱ አቅርቧል።

እስካሁኑ ድረስ በችሎቱ ቆይታ መሠረት የሜጄር ጄኔራል ሃድጎን ሰነድ ከፀሃፊያቸው በማሸሽ ወንጀል የተጠረጠሩት የሜቴክ የሆሚቾ አሚዩኔሽን ኢንጂነሪግ ሰራተኛ የሆኑት ኮሎኔል ሰጠኝ ካሕሳይ፥ በማይመለከታቸው ስልጣን ጣልቃ ገብተው ፀረ ታንክ ላይ የሚገጠም እቃን አላግባብ እንዲገዛ በማድረግ መጠርጠሩን ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪው የሜቴክ የህግ ክፍል እንዳይገዛ ያስቀመጠውን ትዕዛዝ በመተላለፍ 15 ሚሊየን 783 ሺህ 750 ብር ግዥ በመፈጸም፥ የህዝብና የመንግስት ሃብት ያለአግባብ እንዲባክን በማድረግ እንደጠረጠራቸውም ነው ፖሊስ ለችሎቱ ያስረዳው።

የተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ኮሎኔል ካህሳይ ከዚህ በፊት ሰነድ በማሸሽ የተጠረጠሩ መሆኑንና በዚህም ዋስትና መጠየቁን በማስታወስ ፥ አሁን ፖሊስ እያቀረበው ያለው ክስ አዲስ  በመሆኑ ሊካተት እንደማይገባና  በመጀመሪያ ክስ የጠየቀው ዋስትና ይፈቀድ ሲል ጥያቄ  አቅርቧል።

ፖሊስ በበኩሉ በምርመራ ወቅት አዳዲስ ግኝት እንደሚኖርና የዛሬውም በምርመራ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ፥ ዋስትና ሊፈቀድ አይገባም ብሏል ።

ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ ሰነድ ሊያሸሹና ምስክር ሊያባብሉ ስለሚችሉ የዋስትና ጥያቄውን በጥብቅ ተቃውሟል።