ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲቆም የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች በኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተካሄዱ

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ እያጋጠመ ያለውን ችግር ተከትሎ በአካባቢው ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲቆም የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተካሄዱ።            

ሰላማዊ ሰልፎቹ በዛሬው እለት በአምቦ፣ ጊምቢ፣ ሆለታ፣ ቡራዩ፣ ባኮ እና መቱን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞች ነው የተካሄዱት።

በሰላማዊ ሰልፎቹ ላይም በክልሉ በተለያዩ አዋሳኝ አካባቢዎች በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና ማፈናቀል ይቁም፣ ይህንን ተግባር የፈፀሙ አካላት ለህግ ይቅረቡ የሚሉ  እና ሌሎች መፈክሮችን ሰልፈኞቹ ያሰሙ ሰሆን፥ ተግባሩንም አውግዘዋል።

የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫም፥ በተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ያለምንም ችግር መጠናቀቃቸውን አስታውቋል።

በሁሉም ስፍራ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በዋናነት የተነሱት ጥያቄዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና ማፈናቀል ይቁም የሚሉ እና ተግባሩን የሚያወግዙ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል።

ቢሮው ባወጣው መግለጫ፥ በምእራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር እንዲቆም የኦሮሚያ ክልል ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር እየሰራ ቢሆንም የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት በተቀናጀ መንገድ በስልጠና እና በተለያየ ጦር መሳሪያ በመደገፍ በህዝቡ ላይ ጦርነት የከፈቱ በመሆኑ ችግሩን በአጭር አልቆመም ብሏል።

በዚህም መሰረት በአካባቢው ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር መቅረፍ እንዲቻል በሁለቱ ክልሎች ስምምነት እና የብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የፌደራል የፀጥታ አካላት ችግር ባጋጠማቸው አካባቢዎች በመግባት እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን ቢሮው በመግለጫው አመላክቷል።

እስካሁን በተወሰደው እርምጃም ከ100 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ቢሮው አስታውቋል።

በምዕራብ በኩልም ይሁን በሌሎች አካባቢዎች እያጋጠመ ካለው የፀጥታ ችግር ጀርባ ለዓመታት ህዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩና አሁን በሀገሪቱ በተጀመረው ለውጥ ምክንያት መንገድ ሲዘጋባቸው ወደ ስልጣን ተመልሰው ህዝቡን ሊያሰቃዩ እየተጣጣሩ ያሉ ጠላቶች እጅ እንዳለበት ህዝቡ መቼም ቢሆን መዘንጋት እንደሌለበትም መግለጫው አመልክቷል።

ስለዚህም ህብረተሰቡ መንግስት ሰላም እንዳይሰፍን እያደረጉ ያሉ አካላት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ እንዲፋጠን በማድረግ እና በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና መፈናቀል እንዲቆም ከፀጥታ ሀይሉ ጎን በመቆም ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪውን አስተላልፏል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስትም እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አስመልክቶ በየጊዜው ለህዝቡ መረጃ የሚያቀርብ መሆኑንም ተገልጿል።( ምንጭ:  የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)