ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያየ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይተዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ በሌሎች ረቂቅ አዋጆች ላይ በመወያየት ውሳኔዎችን ማሳለፉን የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በውይይቱም የማሻሻያ አዋጁ ከዚህ ቀደም በተቋሙ ላይ ቅሬታ ይቀርብ የነበረውን ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ የማስፈጸም አቅም ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ እንደታመነበት ተነስቷል።

እንዲሁም ተቋሙ በሚያከናውናቸው የክትትል እና የቁጥጥር ስራ ላይ የሚስተዋሉ እክሎችን ለመቅረፍ የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል።

በተጨማሪም የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም በተቋሙ የማቋቋሚያ አዋጅ ውስጥ ያልነበሩ እና የተቋሙን አሠራር የሚያሻሽሉ በርካታ ድንጋጌዎች እንደተካተቱም ተብራርቷል።    

በረቂቅ አዋጁ ላይ የተወያየው ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 7/2011 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ለህግ፣ ፍትህ፣ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በተጨማሪም የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለልማት ፖሊሲ ፋይናንስ ማስፈፀሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ሪፖርት አቅርቧል።

ምክር ቤቱም የብድር ስምምነቱን ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን በአንድ ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በእስራኤል መንግስት መካከል የተደረገውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ ለከተማልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግስት እና በፈረንሳይ ሪፐብሊክ መንግስት መካከል የተደረገውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምፅ ለከተማልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

በኢፌዴሪ መንግስት  እና በሞሮኮ ንጉሳዊ መንግስት መካከል የተደረገውን በኢንቨስትመንት ማስፋፊያ እና ጥበቃ ዘርፍ የትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በወናነት ለውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በተባባሪነት ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ተመርቷል፡፡ (ኤፍ.ቢ.ሲ)