10 ሺ ሰዎች የተሳተፉበት የቡና ማፍላት ሥነሥርዓት በመስቀል አደባባይ ተካሄደ

10ሺ ሰዎች የተሳተፉበት የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓት በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ተካሄደ ።

13ኛው  የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ምክንያት  በማድረግ  በአዲስ አበባ የተለያዩ  ሁነቶች  እየተካሄዱ ሲሆን  በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ የተካሄደው  የቡና ማፍላትና መጠጣት  ሥነ ሥርዓት የበዓሉ  አንዱ አካል  እንደሆነ ተገልጿል ።

“ ኑ ለሰላም ቡና  እንጠጣ ” በሚል  ሐሳብ  በተካሄደው መርሃ ግብር ላይ  ከ10 ሺህ በላይ  የሆኑ ሰዎች  የተሳተፉ ሲሆን  በጋራ  ስለሰላም እየተወያዩ  የቡና መጠጣት ሥነሥርዓት  ተከናውኗል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ  የተገኙት የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ  እንዳሉት  አዲስ አበባ  የሁሉም  የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  መገኛና ትንሿ  የኢትዮጵያ ተምሳሌት ነች ብለዋል ።

 የአንድነታችን በሚገለጽባት የአዲስ  አበባ ከተማ  የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓት  ማከናወናችንም  ታላቅ ትርጉም  ያለው ተግባር ነው  ብለዋል ዶክተር ሰለሞን ።

የአዲስ አበባ  ምክር ቤት አፈጉባኤ  ወይዘሮ አበበች ነጋሽ  በበኩላቸው  የዘንድሮ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የሚከበረው  ልዩነታችንን አጥብበን አንድነታችንን አጠናክረን  መቻላልና  እርቅን መነሻ  በማድረግ የምናከብረው በዓል  ነው ብለዋል ።

በተጨማሪም  ቡና  የኢኮኖሚ ምንጭ ብቻ ሳይሆን በጋራ  ቁጭ  ብለን  የጋራ  ችግራችንን ለመፍታት  የምንጠቀምበት  ታላቅ ባህላዊ  እሴታችን መሆኑን ወይዘሮ አበበች ገልጸዋል ።

የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓቱ ላይ  የተገኙ  ታሳታፊዎች  ለዋልታ እንደገለጹት  ቡና እየጠጣን  ችግሮችን   በጋራና በውይይት  እንፍታ በማለት  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።