አብዴፓ በተሸኙ ነባር አባላት ምትክ አዳዲስ ተተኪ አመራሮችን እየመረጠ ይገኛል

የአብዴፓ ሰባተኛ መደበኛ ጉባዔ  በአራተኛ ቀን ውሎው በተሸኙ ነባር አባላት ምትክ አዳዲስ ተተኪ አመራሮችን እየመረጠ ይገኛል፡፡

ጉባዔው ዛሬ ረፋድ ላይ 50 አመራሮችን የመረጠ ሲሆን፥ የተቀመጡ መስፈርቶችን የሚያሟሉ የ45 የድርጅቱን አዳዲስ አመራሮች ምርጫ ያፀድቃል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የምርጫው መስፈርት የፖለቲካ ተሳትፎ እና አቅም ያለው፣ የድርጅቱን ህግና ደንብ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ በፀረ ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም በሌብነት እና ዘረፋ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያልተሳተፈ፣ አሁን ያለውን ሃገራዊ ለውጥ በቅጡ የሚረዳ አመራር መሆን እንደሚጠበቅበት የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም አዲሱ የአብዴፓ አመራር አካባቢውን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ እና ተግባር አውጥቶ በቁርጠኛ አፈፃፀም የሚተገብር፣ የተሰጠውን ተልዕኮ በግምባር ቀደምትነት የሚያከናውን መሆን እንደሚጠበቅበት በመስፈርቱ ተጠቅሷል፡፡

የትምህርት ዝግጅት፣ ስነምግባር፣ የሴቶች ተሳትፎ እና የዞኖች ተዋፅዖ መመዘኛው ያካተታቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ጉባዔው ዛሬ ከሰዓት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ የምርጫው ውጤት ነገ ጧት ይፋ ይሆናል ተብሏል፡፡(ኤፍቢሲ)