የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረዉ የሪፎርም ስራ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከማስከበር አንፃር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረዉ ተገለጸ

የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረዉ የሪፎርም ስራ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከማስከበር አንፃር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡

የዓለም የሰብዓዊ መብት ቀንና የሰብዓዊ መብት ቻርተር የተፈረመበት 70ኛ ዓመት በዓል በኢትዮጵያ ተከብሯል።    

ሀገሪቱ በቅርቡ እያካሄደች ባለው የለዉጥ ሂደትም ለሰብዓዊ መብት መከበር ትኩረት ሠጥታ በመስራት ላይ እንደሆነችም በዓሉን አስመልክቶ በተካሄደዉ ዉይይት ላይ ተገልጿል።

ፕሮግራሙን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር የምስራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር ያዘጋጀዉ ሲሆን “ኢትዮጵያን ከአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መግለጫ አንፃር ስንመለከት” የሚል መሪ ቃልም ተሰጥቶታል።

የበዓሉ አላማም በኢትዮጵያ ያለዉን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አፈፃፀም ለመገምገምና እየመጡ ያሉ ለዉጦችን ለመለየት በማሰብ ስለመሆኑ ተነግሯል።

በበዓሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገራት ተወካዮችና ሌሎች አካላት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ከሊግ ኦፍ ኔሽንስና ከተመድ ምስረታ ጊዜ ጀምሮ የሰዉ ልጆች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷን አንስተዋል።

በተጨማሪም መንግስት የጀመረዉ የሪፎርም ስራ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት ከማስከበር አንፃር ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረዉ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት ሚስ ንዋኔ ቭዌዴ ኢትዮጵያ በጀመረችዉ የለዉጥ ሂደት በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ አተኩራ መስራቷ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዉ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት መግለጫ እኤአ በ1948 መፅደቁን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከሁለት አመታት በኋላ እኤአ በ1950 ባካሄደዉ ስብሰባዉ ሁሉም አባል ሀገራትና ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ አካላት በየአመቱ ዴሴምበር 10 አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን አድርገዉ እንዲያከብሩት ዉሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።

የ70 አመታት ጉዞን የሚያመላክት የስዕል አዉደ ርዕይም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ለታዳሚያን ቀርቧል።