ወጣቶች በግብረ ገብ ታንጸው ለሀገር ልማት እንዲተጉ መሰራት እንደሚገባ ተገለጸ

ሰላምን ከሰው አስተሳሰብና ባህል ግንባታ ጋር በማያያዝ ወጣቶች በግብረ ገብ ታንጸው ለሀገር ልማት እንዲተጉ በትኩረት መሰራት እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ ከዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የሰላም አምባሳደሮች ጋር  በሰላም ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ውይይት ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ወጣቱ በመልካም ስነ ምግባርና ግብረ ገብ የታነጸ እንዲሆን በትኩረት ይሰራል፡፡

“ስለ ሰላም ማውራት በእናቶችና በሴቶች ያምራል፤ ከእናቶችና ሴቶች የሚመጣውን መልዕክት ሁሉም ይሰማል ያከብራልም” ብለዋል፡፡

ዛሬ ለደረሰቡት ደረጃ ከፈጣሪ ቀጥሎ ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረጉት እናታቸው እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ሚሊዮን የሰላም አምባሳደሮቹንም እንደናታቸው በማየት የጣሉባቸውን አደራ እንደሚቀበሉ አስታውቀዋል፡፡

የመንግስት መዋቅር በዓመቱ ሲደራጅ ሰላምን በማስቀደም የሰላምና የፀጥታ ቢሮ በሚል ማዋቀር ያስፈለገበት ምክንያት የሰላምን አንገብጋቢነት በመረዳት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሰላምን አስመልክቶ ከቤት ጀምሮ በግብረ ገብ የታነጸ ትውልድ በመፍጠር እንደሚሰራ ጠቁመው “እኛም ይህን አደራ ተቀብለን በክልሉ ውስጥ እናቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን በሰላም እጦት ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይሠራል” ብለዋል፡፡

ሰላም ከሰው አስተሳሰብና ከባህል ግንባታ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለዚህም መንግስት የማስተባበር ሥራና የኃይማኖት አባቶችም በየቤተ-እምነታቸው ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አብሮ መኖርና መቻቻልን የሚያጸና ባህል እንዲጎልብት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡

ከሰላም አምባሳደር ቡድኑ አባላት መካከል  ወይዘሮ  አዱኛ አህመድ በበኩላቸው ” በኛ ባህል መሠረት እናት ያለችውን ሁሉም ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጋሉ” ብለዋል፡፡ 

ማንኛውም ሰው ከእናት ነውና የተወለደው ጠቅላይ ሚንስትርም ፕሬዝዳንትም ቢሆን ከሌሎች አካላት በላይ እናቱን ሰምቶ ወደ ተግባር በመግባት ለለውጥ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ሌላዋ የሰላም አምባሳደር ቡድኑ አባል ወይዘሮ  አብነት አዳነ እንደገለጹት ሰላም ሲኖር ሁሉም ነገር ይኖራል ሰላም ለሰው ልጅ በህይወት የመኖርና ለሀገር ህልውና መሰረት  ነው፡፡

“ለሰላም ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል ትልቅ ስራ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል፡፡

በተለይ በኮንሶ፣ በጉራጌ፣ ባስኬቶና ሌሎች አካባቢዎች የሚታየውን የሰላም እጦት ለመፍታት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

56 ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያሉባት የትንሿን ኢትዮጵያን ሰላም ለማረጋገጥ ርዕሰ መስተዳድሩ ያለባቸውን ኃላፊነት በመረዳት በተለይ በወጣቶች ዙሪያ ባሉ አደረጃጀቶች በመጠቀም በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በሐዋሳ ያደረገው  ቆይታ በማጠናቀቅ ትላንትና ወደ ዘጠነኛው ክልል ቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ አቅንተዋል ፡፡(ኢዜአ)