የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማስጠበቅ መተሳሰብና በጋራ መስራት ያስፈልጋል – አቶ ለማ መገርሳ

የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማስጠበቅ መተሳሰብና በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከሀይማኖት አባቶች፤ ሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት አካሂደዋል።

በውይይታቸው ላይ እንደተመለከተው በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ድንበርን ተገን አድርገው የሚነሱ ግጭቶች አግባብነት እንደሌላቸው አቶ ለማ መገርሳ ሰላምን ለማረጋገጥ መደማመጥና መግባባት ያሻል ብለዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ምሁራንን ያካተተ ሀገራዊ ቡድን ተቋቁሞ በሀገር ሰላምና አንድነት ላይ የተጠናከረ ስራ ለማከናወን በጥምረት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ 

ጥምረቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከመስተዳደር አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ለሰላም እጦትና ለተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም ይሰራል፡፡

የሀገር አንድነትና ሰላም ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑ እርስበእርስ ከመተሳሰብ ባለፈ ሕግንም ማክበር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶች የቤት እምነታቸውን አስተምህሮ በተገቢው መንገድ በማስተማር እንዲሁም የሀገር ሽማግሌዎች የህይወት መንገዳቸውን ለወጣቱ በማስተማር ለሀገር ሰላምና አንድነት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ገልፀዋል። የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠልም ሁሉም ባለድርሻ አካል ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ሚናውን እንዲወጣ  ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡