የመከላከያ ሠራዊት ባካሄደው መሠረታዊ የአሰራር ማሻሻያ ስድስት የነበረውን ዕዝ ወደ አራት ዝቅ ማድረጉን አስታወቀ

የመከላከያ ሠራዊት ባካሄደው መሠረታዊ የአሰራር ማሻሻያ ስድስት የነበረውን ዕዝ ወደ አራት ዝቅ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በማሻሻያው የተዋቀሩት አራቱ ዕዞች የሰሜን፣ የደቡብ፣ የምሥራቅና የምዕራብ ዕዞች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ከዚህ በፊት የነበረው የክፍለ ጦርና የብርጌድ ቁጥርም ዝቅ ያለ ሲሆን በተሻሻለው መዋቅርም ብቃት ያላቸው ክፍለ ጦሮችና ብርጌዶች ተደራጅተዋል።

እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ የምድር ኃይል፣ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል፣ የአየር ኃይልና የባህር ኃይል በመሠረታዊ የአሰራር ማሻሻያው እንዲደራጁ ተደርጓል።

የልዩ ዘመቻዎች ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሞላ ኃይለማርያም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማሻሻያውን መሠረት በማድረግ ሁሉንም ብሔሮች የሚወክል አዳዲስ አመራር ምድባ መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

የባህር ኃይልን ለማደራጀት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ሌተናል ጄኔራል ሞላ ጥናቶችን እና ሌሎች ተግባራትን  የሚያከናውን ቡድንም መደራጀቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የምድር ኃይል በቅርብ ጊዜ እንደሚደራጅ ያሉት ሌተናል ጄኔራሉ በዚህም ሳይንሳዊ አደረጃጀት ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በአስተማማኝ ሰላም ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ከፍተኛ ሠራዊት ወደ ተለያዩ ቦታዎች እንዲመደብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ (ኢዜአ)