ወላጆች ልጆቻቸው በተሳሳተ መረጃዎች ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የቅርብ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቆመ

ወላጆች ልጆቻቸው በተሳሳተ መረጃዎች ወደ አላስፈላጊ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የቅርብ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ተጠቆመ ፡፡                              

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እየታየ ያለውን የፀጥታ ችግር ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል የሰላም ኮንፈረንስ በድሬደዋ ከተማ ተካሂዷል ።

ከዚህ ቀደም የነበረውን በሰላምና በአንድነት ተቻችሎ የመኖር እሴቱን ለማጎልበት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ  ለማስቻል ነው የሰላም ኮንፈረንሱ  የተካሄደው፡፡   

በህብረተሰቡ ዘንድ መግባባት መፍጠርን ዓላማ በማድረግ ባለፉት 12 ቀናት በአስተዳደሩ በከተማና በገጠር ቁጥራቸው ከ57 ሺህ በላይ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የሆኑበት የሰላም ኮንፍረንሶች ነው የተካሄዱት፡፡ 

የአስተዳደሩ ከንቲባና ምክትል ከንቲባ እንዲሁም የድርጅት ኃላፊዎች የሚመሩት የሰላም ኮንፍረንስ ማጠቃለያ መድረክ በትናንትናው እለትም ተካሂዷል፡፡

በዚሁም የሰላም ኮንፍረንስ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ድሬዳዋ የበርካታ ብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የሚኖሩባት ከተማ እንደመሆኗ መጠን ሁሉም ነዋሪ በአንድነት፣ በመቻቻል ለሰላሙ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባው ተገልጿል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው በተሳሳቱ መረጃዎች ወደ አላስፈላጊ ችግሮች ውስጥ እንዳይገቡ የቅርብ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባም በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

የአስተዳደሩ ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን ባለፉት ጊዜያት በአስተዳደሩ በከተማም ሆነ በገጠር ነዋሪውን ህብረተሰብን  የማይወክሉ አካላት የተለያዩ ጉዳቶች እንዲደርሱ ያደረጉ ሲሆን ይህም ችግር ከዚህ ቀደም ተከስቶ እንደማያውቅና ከተማዋንም የማይወክል ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ የለውጥ ስራዎች እንደተሰሩና በቀጣይ ነዋሪው ህብረተሰብ ሰላሙን በማስጠበቅና አንድነቱን በማጠናከር ችግር ፈጣሪ የሆኑ አካላትን ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሆን ለህግ ሊያቀርቡ እንደሚገባ ከንቲባው አሳስበዋል፡፡ 

በሰላም ኮንፍረንሱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን ኮንፍረንሱ ማጠቃለያም ባለ-ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡ (ምንጭ፡-ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መ/ኮ/ጉ/ ቢሮ)