ጦር መሣሪያ ይዘው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ከሞከሩት የሠራዊት አባላት መካከል 66ቱ ተቀጡ

ከወራት በፊት ከነ ጦር መሣሪያቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ሙከራ አድርገው ከነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል በ66ቱ ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉ ተገለጸ ።

የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ባለፈው መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም  የጦር መሣሪያቸው ይዘው ጥያቄያቸውን ለማቅረብ  ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ሙከራ አደርገው እንደነበር ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትር  ጽህፈት ቤት ለመግባት  ከሞከሩት ወታደሮች መካከል በ66ቱ ላይ በቀዳማይ ወታደራዊ ፍርድ ቤት አማካኝነት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል።

የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ዘውዱ በላይ ዛሬ በሠጡት መግለጫ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ ከነ ጦር መሳሪያቸው ወደጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለመግባት ያደረጉት ሙከራ የሠራዊቱን ክብር የሚቀንስ በመሆኑ የቅጣት እርምጃው ተወስዷል።

”ማንኛውም ኃይል ወደ ቤተ መንግስት የሚገባው በምርጫ ብቻ እንጂ በጦር መሳሪያ በማስገደድ መሆን የለበትም ብሎ የሚታገል ሠራዊት ነው ያለው” ብለዋል።

ወታደራዊ ፍርድ የተላለፈባቸው የሠራዊቱ አባላት የፈጸሙት ተግባር የመከላከያ ሠራዊት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያገኘውን ክብር የሚቀንስ እንደሆነም ነው ሜጀር ጀነራል ዘውዱ ያብራሩት።