ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከ30 የሚበልጡ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው የተወያዩት አምባሳደሮቹ ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በእርሳቸው አመራር ስር ያስመዘገበችውን ለውጥ በጥሩ ጎኑ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

በተለይም የፖለቲካ ምህዳር መስፋትና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ዙሪያ የታዩትን እመርታዎች እንዲሁም አገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጸጥታና ውህደት ዙሪያ እየተጫወተች ያለውን ሚና እንደሚያደንቁ መግለጻቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ከዚህም በመነሳት የአውሮፓ ህብረት አባልና አባል ያልሆኑ አገራት አምባሳደሮቹ በአንድ ድምጽ ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል። (ምንጭ፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)