ምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ምክክር ተደረገ

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግና የፍትህ አማካሪ ጉባዔ ፅህፈት ቤት ምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም ባወጣው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ሲቪክ ማህበራት ጋር  ምክክር አድርጓል፡፡

ረቂቅ አዋጁ እንደገና የተዘጋጀውም ምርጫ ቦርዱ ከዚህ በፊት የነበሩበትን ክፍተቶች በማሻሻል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችን በእኩል እንዲያሳትፍ ለማድረግ እና የአፈፃፀም ብቃቱን ለማሳደግ ታስቦ ነው ተብሏል።

ለምክክር የቀረበው የምርጫ ቦርድን መልሶ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ከዚህ ቀደም የወጣውን አዋጅ 532/99 በማሻሻል በቀጣይ የሚዳበሩ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን በውስጡም አራት ምዕራፎችና 32 አንቀጾች እንደተካተቱበት ተገልጿል፡፡ 

አዋጁ እንደ አዲስ የሚቋቋመውን ቦርድ ዓላማ፣ ኃላፊነትና ተግባርን አካቶ የተዘጋጀ ሲሆን የቦርዱ አባላት የስራ ድርሻም በጽህፈት ቤቱ ቴክኒካል ስራዎች ላይ ያተኮረ ይሆናል ነው የተባለው።

በውይይት መድረኩ ላይ በቀረበው በዚህ ረቂቅ  አዋጅ ላይም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሻሻል በሚገባቸው ነጥቦች ላይ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን አዋጁን ለማፅደቅ ህገመንግስቱንና የምርጫ ህጉን ወደ ኋላ ተመልሶ መፈተሽ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ምርጫን የሚያስፈጽም አካል በኮሚሽን ይቋቋም የሚሉ ሓሳቦችም ተነስተዋል፡፡

የጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግና የፍትህ አማካሪ ጉባዔ ፅህፈት ቤት ሰብሳቢ የሆኑት ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ የግብዓት ሓሳቦች ተካተውበት ለአጽዳቂ አካል እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት የቦርዱ አባላት አሰያየም በጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቦ በቀጥታ ለህዝብ ተወካች ምክር ቤት የሚፀድቅ እንደነበር ይታወቃል።

በተሻሻለው ረቂቅ ላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘጠኝ አባላትን የያዘ ገለልተኛ ኮሚቴ ያዋቅራል።

ኮሚቴውም ለቦርድ አባላት የሚያስፈልገውን የቁጥር መጠን በእጥፍ ጨምሮ በመመልመል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያቀርብ ይደረጋል ተብሏል።

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከመከሩ በኋላ የቦርዱን ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ በመለየት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ የሚያፀድቅ ይሆናል።