የቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ

የቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ለይ  በቅደስት ስላሌ ካቴድራል በክብር ተፈፅሟል።

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና  የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

ከጧቱ ሶስት ስዓት ጀምሮ  በሚሊኒየም  አዳራሽ በርካታ  የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች  በተገኙበት አስከሬናቸው የመሰናበት እንዲሁም  የፍትሃት  ስነ ስርዓቶች   ተከናውነዋል ።

የአዲስ አበባ ህዝብ ከጧቱ ሶስት ስዓት ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ በመገኘትም  የቀድሞ ፕሬዚደንትን አስከሬን የስንብት ስነ ስርዓት ላይ ተሳትፎ  አድርጓል።

በሚሊኒየም አዳራሽ  በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ  የቀድሞ ፕሬዚደንት  ግርማ ወልደጊዮርጊስ  የህይወት ታሪካቸው ለታዳሚያን ተነቧል ።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሚሊኒየም አዳራሽ  ተገኝተው የስንብት ንግግር አድርገዋል።

ከሚሊየኒየም አዳራሽ ጀምሮ የቀብር ስነ ስርዓቱ እስከ ተፈፀመበት ቅድስት ካቴድራል ቤተክርስቲያን ድረስ አስከሬናቸው በክብር ሰረገላ እና ማርሽ ባንድ ታጅቦ በርካታ  ሰዎች በተገኙበት የአሸኛኘት ስነ ስርዓት ተደርጓል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት አስከሬኑ በክብር ቅደስት ስላሌ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እንደደረሰም  በካህናት የመጨረሻ ፍትሀተ ፀሎት የተደረገ ሲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓርቲያርክ ሊቀ  ጳጳስ  አማካኝነት የማሳረጊያ ፍትሃተ ፀሎት ተካሄዷል።

ክብርት ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ፣ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳር፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና የቀደሞው ፕሬዝዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሸመ የአበባ ጉንጉን አኑረዋል ።

በተጨማሪም  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና በፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ፣ የአፍሪካ ሀብረት ዋና ፀሀፊ ሙሳ ፋቂ እንደ ቅደም ተከተላቸው የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ሁሉም የክልል መስተዳድሮች እና የሁለቱ ከተማ አሰተዳደሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የሰላም ሚኒስትር እንዲሁም በርካታ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል።

ከቀኑ በአስር ስዓት ላይ አሰከሬናቸው በተዘጋጀለት ቦታ ላይ በክብር ካረፈ በኋላም  በመጨረሻ መድፍ ተተኩሶ የስነ ሥርዓቱ ተጠናቋል ።

 

የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በህይወት ዘመናቸው ለአገራቸው የሠጡት አገልግሎት ያበረከቱት አስተዋጽኦ  

የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ አገራቸውን ለ12 ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ባገለገሉበት ወቅት በተለያዩ የሰብዓዊ ልማት ስራዎች ላይ በስፋት ይሳተፉ እንደነበር ይታወቃል።

 ክቡር ፕሬዝዳንቱ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እንዲቋቁሞና ወደ ስራ አንዲገቡ ደከምኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከፍተኛ ድጋፍና ትብብር ያደረጉ ታላቅ የአገር ባለውለታ ሰው ነበሩ።

በኢትዮጵያ የሰላም፣ የዲሞክራሲና ህዝባዊ የምክክር መድረክ እንዲጠናከር፤ የኢትዮጵያ የአይን ባንክ የአካል ክፍል ንቅለ ተከላ እንዲመሰረት እና አገልግሎት እንዲሰጥ፤ የአካባቢ ጥበቃና የተፈጥሮ ሀብት ስራ በአገሪቱ እንዲስፋፋ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በራሳቸው ወጪ የሰላም አዳራሽ በማስገንባት በውስጡ የዲጂታል ቤተ መፅሀፍት በማቋቋም ለህዝብ አበርክተዋል ።

 በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎቸ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር አገር አቀፍ የአገር ሽማግሌዎች ማህበር የበላይ ጠባቂ በመሆን ያገለገሉ፤ የአረንጓድ ልማት እድገት እንዲስፋፋ በመላ አገሪቱ የችግኝ ተከላ እና የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች እንዲዘወተሩ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ታላቅ የአገር ባለውልታ ነበሩ።

በክልሉ ሰላም እንዲሰፈን በተለይም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላምና እርቅ እንዲወርድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማደረጋቸው ይታወቃል።