የኦሮ-ማራ ህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር የሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ተባለ

የኦሮ-ማራ ሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር የሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በደሴ ዩኒቨርስቲ እየተካሄደ ባለው 3ኛው ዙር የኦሮ-ማራ የምሁራን ጉባኤ  ላይ  ተገለጸ ።

የወሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ሁለቱ ህዝቦች ከሚያገናኛቸው ይልቅ የሚያለያያቸውንና ያልነበሩ ታሪኮች በመተረካቸው ለ27 ዓመታት ያህል  የሁለቱን ህዝቦች አንድነትን  ጎድቶታል ብለዋል ።

ይሁን እንጂ የሁለቱ ህዝቦች አንድነት ፣ በደምና አጥንት የተሳለሰ በመሆኑ ሁለቱን  ብሔሮች  የማጋጨት ዕቅድ  በሁለቱ ሕዝቦች ትብብር  ከሽፏል ብለዋል ።

የኦሮ-ማራ ምሁራን ጉባኤም  የሁለቱን ሕዝቦች ከሚያራርቃቸው ይልቅ የሚያቀራርቧቸውን  ታሪኮች  በምርምርና በጥናት  በታገዘ መልኩ አንድነታቸውን  ይበልጥ  ማጠናከር  ይቻላል ተብሏል ።

በጉባኤው ላይ በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎችም የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችም ከአጠቃላይ የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር 70  በመቶ የሚሆነውን  የሚሸፍኑ  መሆኑ ተገልጿል ።

የኦሮሞና አማራ ህዝቦች  አንድነትና ትብብርም ለአጠቃላይ  አገራዊ አንድነት  የበለጠ ፋይዳ   እንዳላው  በምሁራን  በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ የተገለጸ ሲሆን የህዝቦቹን  አንድነትና ትብብር የበለጠ ለማጠናከር  የሁለቱ ብሔሮች  ምሁራን ቀዳሚው  ድርሻ ሊወስዱ ይገባል ተብሏል  ።

የኦሮ-ማራ የምሁራን መድረክ ትናንት በወሎ ዩኒቨርስቲ ተጀምሮ  በዛሬው ዕለት በከሚሴ ዩኒቨርስቲ  የቀጠለ ሲሆን  በዛሬው ዕለት  እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል ።

በጉባኤው  ከኦሮሚያ 12  ፣ ከአማራ 10 ፣ ከአዲስ አበባ  7  የዩኒቨርስቲ  ፕሬዚዳንቶች ፣ የሁለቱ ብሔሮች  ምሁራን እንዲሁም የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ባለሥልጣናት ተገኝተዋል ።

3ኛ ጊዜ   የኦሮ-ማራ ጉባኤ  “ የኦሮሞናአማራ ህዝቦች በጋራ የመኖር ታሪካዊ እሴቶች  ፋይዳ በወሎ ህዝብ መገለጫ ”  በሚል  መሪ ቃል  እየተካሄደ ነው ።