በኦሮሚያ ክልል ፀረ-ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ችግር 12 የፖሊስ አባላትና 29 ዜጎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች ፀረ-ሰላም ኃይሎች በፈጠሩት ችግር 12 የፖሊስ አባላትና የ29 ንፁሃን ዜጎች ህይወት ማለፉን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አለማየሁ እጅጉ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ 139 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በዚሁም በቄለም ወለጋ የተገደሉትን 2 የዞን ፖሊስ አመራሮችን ጨምሮ የ12 ፖሊስ አባላት ህይወት ማለፉንና 77 ፖሊሶች መቁሰላቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚደርሰው ጉዳት ከዚህም በላይ ነው ያሉት ኮሚሽን ጀነራሉ የግለሰቦችን ሳይጨምር ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከባንክ መዘረፉን ገልፀዋል።

ታጣቂዎቹ በአካባቢው ካለ ፖሊስ ጣቢያ 2072 ክላሺንኮቭ ጦር መሳሪያ መዝረፋቸውም ነው የተገለፀው።

በምዕራባዊ የክልሉ አካባቢዎች ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር በውይይትና በትዕግስት ለመፍታት መሞከሩን የገለጹት ኮሚሽሩ እስከ ህይወት መስዋዕትነት የደረሰ ዋጋ ማስከፈሉን ተናግረዋል፡፡

በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ በቄለም ወለጋና በምዕራብ ጉጂ ዞኖች የተከሰቱት ችግሮችም በኦነግ የተቀነባበረ እንደሆነ ማወቅ መቻላቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስትም ሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለወራት ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተለዉ እንደነበር የገለፁት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አለማየሁ በአፋጣኝ ወደ እርምጃ ያልተገባውም ያሉትን የሰላም አማራጮች አሟጦ ለመጠቀም በማሰብ ነዉ ብለዋል።

ሆኖም ትዕግስታችን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለን በመሆኑ ከዚህ በኋላ ፖሊስ ኮሚሽኑ የቆመለትን ሰላም የማስከበርና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል። 

በተያያዘም አባ ቶርቤ ወይም ባለሳምንት በሚል መጠሪያ በድብቅ ሰዎችን ሲገድሉና ሲያስገድሉ የነበሩት አካላት ከኦነግ ጋር ግንኙነት አላቸዉ ብለዋል።

እነዚህን አካላት ተከታሎ ለህግ ለማቅረብም የክልሉ ፖሊስ እየሰራ መሆኑን ለዚህም ለሁሉም ዞኖች ጥብቅ መመሪያ መተላለፉን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።