ፍርድ ቤቱ በዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለምፍፁም ላይ የክስ መመስረቻ 10 ቀናት ፈቀደ

ፍርድ ቤቱ በዓለም ገነት ቆርቆሮ ፋብሪካና በግንባታ ላይ ያለው ፎር ፖይንት ሸራተን ሆቴል ባለቤት አቶ ዓለምፍፁም ገብረስላሴ  ላይ  የክስ መመስረቻ 10 ቀናት ፈቀደ።

አቶ ዓለምፍፁም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ የወንጀል ችሎት በትናንትናው ዕለት ቀርበዋል።

መርማሪ ፖሊስ በአቶ ዓለምፍፁም ገብረስላሴ ላይ በተጠረጠሩበት ወንጀል ከአንድ ወር በላይ ሲያካሂድ የቆየውን ምርመራ በማጠናቀቁ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ይህን ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በተጠርጣሪው ላይ የተካሄደውን የምርመራ መዝገብ በትናንትናው እለት መቀበሉን ገልጿል።

አቶ አለምፍጹም ሪቬራ ሆቴልና የፕላስቲክ ፋብሪካን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ጋር ባለ የቅርብ ዝምድናና ጓደኝነት በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ወንጀል ነው የተጠረጠሩት።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሆቴሉ እንዳይገዛ ወስኖ ሳለ 128 ሚሊየን ብር ተስማምተው ውሉ ላይ ግን በ195 ሚሊየን ብር ሸጠዋል፤ 67 ሚሊየን ብር ልዩነቱንም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የወሰዱትን ብድር ከፍለውበታል ብሏል መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ።

ሽያጩ ሲፈጸም የሽያጭ ግብር ለጉሙሩክ በሻጭ መከፈል ቢኖርበትም ገዢው ሜቴክ 15 ሚሊየን ብር እንዲከፍል ተብሎም ውሉ ላይ መፈረሙንም ነው ያስረዳው።

በመሆኑም ግለሰቡ ሽያጩ ያልተገባና ዝምድና ላይ የተመሰረተ በተጋነነ ዋጋ በመፈፀም የህዝብን ገንዘብ ተጠቅመዋል በሚል በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል።

በተጨማሪም የፒቪሲ ፕሮፋይል ፋብሪካ ውስጥ የማይሰሩ ፒቪሲ ታይልስና ፒቪሲ ማት ሁለት ማሽኖች ተጠርጣሪው ለኮርፖሬሽኑ ሲያስረክቡ የማሽኖቹ ዋጋ ተቀናሽ ሳያደርጉ ተቀናሽ ክፍያ በመውሰድ እንዲሁም ከልማት ያለበትን ብድር ከነወለዱ ሜቴክ እንዲከፍል መደረጉ ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ ተጠርጣሪው ከውል ውጭ 44 ሚሊየን 36 ሺህ 203 ብር የመንግስትን ገንዘብ ያለአግባብ ለእራሳቸው ጥቅም ያዋሉና በዚሁ ልክ በመንግስት ላይ ጉዳት ያደረሱ መሆኑን በመጥቀስ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ፓሊስ ምርመራውን አጠናቆ መዝገብ እንዲዘጋለት መጠየቁን ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የክስ መመሰረቻ ጊዜ ይሠጠኝ ማለቱ ደንበኛን በእስር ለማቆየት ሆን ተብሎ የተፈፀመ ተግባር ነው ሲል ተናግረዋል።

የተፈፀመው ወንጀል ሳይሆን ከውል ጋር በተያያዘ የተፈፀመ በመሆኑ ተጠርጣሪው በወንጀል ሳይሆን በፍትሃብሔር መጠየቅ ካለባቸው የሚጠየቁ በመሆኑ ፍርድ ቤቱን በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።

ተጨማሪ የክስ መመስረቻ ጊዜ ምን አልባትም የሚፈቅድ ከሆነ አጠር ያለ ጊዜ እንዲሆን አመልክተዋል።

የግራ ቀኙን ሂደት የተመለከተው ፍርድ ቤት የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ 10 ቀናት በመፍቀድ  አቃቤ ህግን ምላሽ ለማድመጥ ለታህሳስ 26 ቀን 2011 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።(ኤፍቢሲ)