በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ጉዞ ሁሉም ጠብቆ ማቆየት እንዳለበት አርበኞች ግንቦት ሰባት አስታወቀ

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ጉዞ ሁሉም ጠብቆ ማቆየት እንዳለበት አርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ አስታወቀ፡፡

በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ውስጥ የገባው ንቅናቄው ዛሬ በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ዴሞክራሲያዊ ትግሉን ለማስቀጠል ከአመፅ ነፃ የሆነ የሰላማዊ የትግል መንገድን    ብቻ እንደሚከተል ገልጸዋል፡፡

የንቅናቄው ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሠጡት መግለጫ አመፅና ትጥቅን መሠረት ያደረገ ትግል ኢትዮጵያን ወደ ውድመት ከመምራት በስተቀር ሌላ ጥቅም እንደማይኖረው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተፎካካሪ ፓርቲው ጋር ግንኙነት የነበራቸው እና በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የታጠቁ ኃይሎች ወደ መንግስት እንዲቀላቀሉ ከመንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ፀሐፊው አባላቱ በየትኛውም የአመፅ ድርጊት እንዳይሳተፉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፉንም አስታውቀዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ አብዛኛዎቹ ታጣቂዎቹ ትጥቅ መፍታታቸውንና ወደ ካምፕ እንዲገቡ መደረጉን ያስታወቀው አቶ አንዳርጋቸው በኤርትራ የነበሩ ከ300 በላይ ታጣቂዎች እዛው ኤርትራ ትጥቃቸውን መፍታታቸውን እና በሀገር ወስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ500 በላይ ታጣቂዎችም ትጥቅ ፈትተው ወደ ካምፕ መግባታቸውና እየገቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ እና ህግን ማስከበር በዋናነት የመንግስት ኃላፊነት ሆኖ የፖለቲካ ድርጅቶችም አባላቶቻቸውን ለአመጽ በማራቅ መንግስትን ሊያግዙ እንደሚገባ ንቅናቄው በሠጠው መግለጫ ጥሪ አቅርበዋል፡፡