ህዝብን የወገነ አመራር ለውጡን የማስቀጠል አቅም እንደሚኖረው የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ገለጹ

ህዝብን የወገነ አመራር ለውጡን የማስቀጠል አቅም እንደሚኖረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡  

"የተደራጀ እና የተቀናጀ አመራር ለውጡን በብቃት ለመምራት!" በሚል መርህ ቃል በተዘጋጀው የከተማ አስተዳደር አመራሮች የግማሽ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባ ለአመራሮቹ ባደረጉት ንግግር ላይ የበቃ እና ህዝብን የወገነ አመራር ለውጡን የማስቀጠል አቅም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው በተጨማሪም አመራሩ ለውጡን በመቀበሉ ረገድ በግንባር ቀደም መቆም እንዳለበት፣ ለወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል በሚፈጠርበት ሁኔታ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው አመራሩ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ሶስተኛ ቀኑን በያዘው በዚሁ መድረክ ላይ ከ1 ሺህ 500 የሚሆኑ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን በሁሉም ሴክተሮች የታዩ ደካማ አተገባበሮችን በመቅረፍ ህብረተሰብ ተኮር የሆኑ ተግባራት ላይ አተኩሮ መስራት እንዳለበት ተጠቅሷል፡፡

በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ያለው ይህ መድረክ በነገው ዕለት እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡

(ምንጭ፡-የከንተባ ጽህፈት ቤት)