ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከህገ መንግስት ተርጓሚ አካላት ጋር በህገ መንግስት አተረጓጎም ስርዓት ዙሪያ ምክክር አደረገ

ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ከህገ መንግስት ተርጓሚ አካላት ጋር በህገ መንግስት አተረጓጎም ስርዓት ዙሪያ ምክክር አድርጓል።

በምክክር መደረኩ ፍትህን በተሻለ ደረጃ ለማስቀጠል የህገ መንግስት አተረጓጎም ስርአትን ማጠናከር እንደሚገባም ተጠቁሟል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 82 መሰረት የተቋቋመው የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሚወጡ ህጎች ከህገ መንግስቱ እንዳይጋጩ መከታተል፣ በፍርድ ቤቶች በኩል የህገ መንግስት ትርጉም ሲነሳ መርምሮ ትርጉም የሚያስፈልገውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መምራትና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን ተሰጥቶታል።

በተለይ የህገ መንግስት ትርጉም ላይ ዜጎች ከታችኛው ፍርድ ቤት ተነስተው እስከላይኛው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሰው ትርጉም የሚጠየቅበት ሂደትንም ያስተናግዳል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ከህገ መንግስት ተርጓሚ አካላት ጋር በህገ መንግስት አተረጓጎም ስርዓት ዙሪያ ባደረገው ምክክር መድረኩ ላይም የተሻለ ፍትህ ለመፍጠር የህገ መንግስት አተረጓጎም ስርአትም ሆነ ሂደትን በተሻለ መምራት እንደሚገባ ተነስቷል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፥ የተጠናከረ ስራ ለመስራት ተርጓሚው አካል የሚቀርብለት የትርጉም ጥያቄ፥ በትላልቅና ፖለቲካዊ ትርጉም በሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት አለም ላይ 86 በመቶ የሚሆኑ ሀገራት የህገ መንግስት ትርጉም ስልጣንን፣ ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች አልያም ለህገ መንግስት ፍርድ ቤቶች ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያም ህገ መንግስቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ ነው።

ይህም ፍርድ ቤቶች በየደረጃው ህገ መንግስታዊ ትርጉምን መሰረት አድርገው የሚሰጡት ውሳኔ የሚጋፋ ሳይሆን ፖለቲካዊ ትርጉም ሲያስፈልግ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚታይበትን አሰራር የያዘ ነው።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ አሁናዊ ሁኔታው ህገ መንግስት እንዲቀየር የሚያስገድድ ከሆነ ህገ መንግስቱን በማሻሻል ለመቀየር ዝግ አለመሆኑን ተናግረዋል።

አጣሪ ጉባኤው ቀደም ሲል እንደ አንድ የስራ ክፍል ከፌዴሬሸን ምክር ቤት ጋር በመዳበል በተጠናከረና በተሟላ የሰው ሀይል በርካታ አቤቱታዎችን በመቀበል ውሳኔና የውሳኔ ሀሳቦችን በመስጠት እየሰራ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

ከዚህ ባለፈ ግን አጣሪ ጉባኤው በርካታ ችግሮች እንዳጋጠሙት የአጣሪ ምክር ቤቱ አባል አቶ ሚሊዮን አሰፋ ተናግረዋል።

በመድረኩ ማሻሻያዎች እስከሚመጡ ድረስ የህገ መንግስት አተረጓጎም ስርአትን በማጠናከር የተሻለ ፍትህን መፍጠርን መሰረት ያደረገ ስራ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)