የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከፕሬዝዳንት አልበሽር ጋር በሁለትዮሽና የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ጋር በሁለትዮሽና ክልላዊ በሆኑ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የሱዳንና የኢትዮጵያ ህዝቦች ከአንድ ምንጭ ከሚፈልቅ የአባይ ወንዝ ውሃ በጋራ የሚጠጡ፣ በመከራም ሆነ በደስታ ጊዜ ለዘመናት አብረው የኖሩና ወደፊትም አብረው የሚቀጥሉ ወንድምና እህት ህዝቦች መሆናቸውን በውይይታቸው አስምረውበታል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው የሚኖሩ ያህል እንዲሰማቸው እንደሚፈልጉና የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ከሱዳን የአገራዊ ደህንነት ጉዳይ ጋር የተያየዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ወቅርነህ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸው ከወራት በፊት ከአንድ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሱዳን የተለያዩ እስር ቤቶች በነፃ መለቀቃቸው የሁለቱን አገራት ህዝቦች እና የእርስ በእርስ ግንኙነት መጠናከርን ያሳያል ብለዋል።

ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት በአፍሪካ ቀንድ የኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት እና የአህጉራዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፋፋት በአንድነት ተባብረው ለመስራት መስማማታቸው ይታወቃል።

ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልባሽር በዚህ ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው፡፡

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተላከ መልዕክት ለሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ማድረሳቸውም ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)