በክልሉ በአምስት ዞኖች በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት 810 ትምህርት ቤቶች ትምህርት ማቋረጣቸው ተገለጸ

በኦሮሚያ አምስት ዞኖች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች 810 ትምህርት ቤቶች መደበኛውን  የመማር ማስተማር ስራ እያከናወኑ እንዳልሆነ  የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ ።

የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት  በምስራቅ ወለጋ 290 ፣በቄለም ወለጋ 296፤ በሆሩ ጉድሩ ወለጋ 114፣ በምዕራብ ጉጂ 66 እንዲሁም በቦረና 44 ትምህር ቤቶች ስራቸውን አቁመዋል፡፡

በተጨማሪም በምዕራብ ወለጋ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች 955 ለዘጠኝ ቀናት ተዘግተው የቆዩ ቢሆንም ህብረተሰቡ እና መምህራን ባደረጉት ርብርብ ወደ መማር ማስተማር ተግባራቸው መመለሳቸውን ጠቁመዋል፡፡  

በኦሮሚያ ክልል ሌሎች የክልሉ ዞኖችም ይህን መልካም ተግባር ወስደው በአፋጣኝ ሥራቸውን እንዲጀምሩ የቢሮው ኃላፊ ዶክተር  ቶላ በሪሶ አሳስበዋል።

ዶክተር ቶላ ከክልሉ የፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ወጣትም ሆነ ተማሪ ትግልና መስዋዕትነት ባስፈግ ጊዜ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ አሁን የመጣውን ለውጥ ማምጣቱን  አብራርተዋል ።

በኦሮሚያ ክልል የሚፈለገው ለውጥ በመምጣቱ ከዚህ በኋላ ትግሉ ድህነትና ማሃይምነትን ለማጥፋት  መሆን እንደሚገባውም አንስተዋል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎችም ብቸኛው ሥልጣን ማግኛ መንገድ ሰላማዊ ትግል መሆኑን ተረድተዉ የክልሉን የመማር ማስተማር  ሥርዓትን ከማወክ እንዲቆጠቡና ይልቁንም አጋዥ ሚና ሊጫወቱ  እንደሚገባ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።