በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የተገባው ቃል ተግባራዊ አለመደረጉ ተገለጸ

በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ አለማድረጉ ተገለጸ፡፡

የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ከይርጋ ጨፌ ከተማና ወረዳ አስተዳደር ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች እና ሰላም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ዞን በተከሰተው ግጭት ምክንያት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው የተመለሱ የጌዴኦ ብሔረሰቦች በመንግስት በኩል ድጋፍ ተደርጎላቸው ቀድም ሲል  ከተፈናቀሉበት ስፍራ መልሶ እንዲቋቋሙ ለማድረግ ቃል ቢገባም ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጸዋል፡፡

የፌደራል እና የክልል መንግስት ችግራችንን አልሰሙንም ያሉት ነዋሪዎቹ ችግር ፈጣሪዎችን ለህግ ከማቅረብ ይልቅ የተሻለ ቦታ እየተሰጣቸው ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ በበኩላቸው መንግስት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የገባውን ቃል ተግባራዊ አለማድረጉን በውይይቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም በተከሰተው ግጭት ምክንያት የዞኑ ተወላጆች ወደ ስፍራቸው እንዲመለሱ ቢደረግም አሁንም ችግር ላይ መሆናቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የደኢህዴን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው በተለይም የኦሮሚያ እና የፌደራል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ፈጥነው መስራት አለባቸው ሲሉ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ የዞኑ ምሁራን እና የኃይማኖት አባቶች መንግስት ስርዓት ሲጣስ ዝም ማለቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በምዕራብ እና ምስራቅ ጉጂ ዞን በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ከ8 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡