የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ በቅርቡ ፀድቆ ወደ ስራ ይገባል- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

መስሪያ ቤቱ የ2011 በጀት ዓመት የአምሰት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ላይ ይገኛል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ በርሃኑ ፀጋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉትም፥ ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በመፅደቅ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ረቂቅ የማሻሻያ አዋጁ የመደራጀት መበትን የተመለከቱ ዓለም አቀፋዊ እና ህገ መንግስታዊ መርህዎችን ባገናዘበ መልኩ መዘጋጀቱን ዋና አቃቤ ህጉ ተናግረዋል።

 

የፀረ ሽብር አዋጅንም ለማሻሻል ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት የተጠናቀቀ በመሆኑም በቅርቡ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል ነው ያሉት።

በተጨማሪም የስነ ስርዓትና ማስረጃ አዋጅ፣ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር አዋጅ፣ የንግድ ህግ፣ የጦር መሳሪያ አያያዝና አስተዳደር አዋጅ፣ የምርጫ ህግ፣ የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ እና የሀይል አጠቃቀም አዋጅን ለማሻሻል የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆች በውይይት መድረኮች ዳብረው እንደሚቀርቡ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ከፍትህ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅት አለመኖር፣ ከፖሊስ ጋር ቅንጅታዊ አሰራር አለመዳበር እና የሰው ሀይል ብቃትና የስነ ምግባር መጓደል ባለፉት አምስት ወራት ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ በሪፖርታቸው አንስተዋል።  (ምንጭ፡ ኤፍ.ቢ.ሲ)