በኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች ያጋጠመውን የሰላም መጓደል ለመቅረፍ በነቀምቴ ከተማ ውይይት እየተካሄደ ነው

በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች ያጋጠመውን የሰላም መጓደል ለመቅረፍ በምስራቅ ወለጋ ዞንና በነቀምቴ ከተማ ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በምስራቅ ወለጋ ዞንና በነቀምቴ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይትም ሰላምን በተመለከተ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው መንሸራሸራቸው ተገልጿል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስት እያደረገ ያለውን ለውጥ ተገንዝበው መጓዝ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶች ተቀራርበው ባለመሥራታቸው ህዝቡን ለጉዳት እያጋለጡ መሆኑንም በውይይቱ እየተሳተፉ የሚገኙ የምስራቅ ወለጋ ዞን የመንግስት ሠራተኞች ገልፀዋል።

በዚህም በክልሉ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎች ለላቀ ተግባርና ሰላም መስማማት እንደሚገባቸው አንስተው ፓርቲዎቹ ህዝብን ለማገልገል አስበው ለአንድ ዓላማ የቆሙ ከሆነ መደማመጥ አለባቸው ሲሉ የመንግስት ሠራተኞቹ  ጠቅሰዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ረታ በላቸው በበኩላቸው፤ ህዝቡን ለመጥቀም የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላማዊ መንገድ መከተል መብታቸው ሳይሆን ሃገራዊና ህዝባዊ ግዴታቸው ነው ብለዋል።

ምክትል ኮሚሽነሩ እንደገለጹት ባለፉት ወራት በርካታ ፓርቲዎች ስምምነት መፈጸማቸውን አስታውሰው ስምምነታቸው ግን ሙሉ መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሰላምን ለማስፈን የሁሉም ህብረተሰብ ድርሻ በመሆኑ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በትናንትናው ዕለትም የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ ከወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በተደረገው ውይይትም ህብረተሰቡ ማህበራዊ ህይወቱ ሳይስተጓጎል ልጆች በሰላም ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የንግድ እንቅስቃሴ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የህብረተሰቡን ሰላምና ፍላጎት በመገንዘብ ወደ መፍትሔ እንዲመጡ አሳስበዋል፡፡ (ኤፍ.ቢ.ሲ)