የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ 530 ታራሚዎች ይቅርታ ሊደረግላቸው መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ

የዘንድሮውን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ 530 ታራሚዎች ይቅርታ እንደሚደረግላቸው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡

በይቅርታ እንዲፈቱ ዕድሉን ያገኙት በፌደራልና በክልል መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሥር ያሉ ታራሚዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ መንግስት በሠጠው ይቅርታ ህፃናት ያላቸው እናቶች ቅድሚያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን መንግስት ከሰጠው ምህረት በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በወጣው የምህረት እዋጅ እስካሁን 13 ሺህ 122 ሰዎች ተጠቃሚ በመሆን የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን አቶ ዝናቡ ተናግረዋል፡፡

ሰላም፣ አንድነትንና የለውጥ ሂደቱን ለማስፋት ሲባል ከሐምሌ 13 ፣2010 ጀምሮ ተግባር ላይ የዋለው የምህረት አዋጅ የፊታችን ጥር 13፣2011 እንደሚጠናቀቅም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

አዋጁን ተከትሎ በውጭ አገራት ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መግባት ችለዋል፡፡

ከቡራዩ ጥቃት ጋር በተያያዘም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች ምርመራው ተጠናቆ በ109 ተጠርጣሪዎች ላይ በዛሬው ዕለት ክስ መመስረቱን ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡

ክስ ከተመሰረተባቸው ውስጥ 28 ያህሉ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል፡፡

ባልተያዙትና ክስ የተመሰረተባቸውን ተጠርጣሪዎች ፖሊስ መያዣ በትኖ በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡