የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በሁኔታዎች የማይለዋወጥ መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ

የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በሁኔታዎች የማይለዋወጥ መሆኑን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ፡፡

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የጊዜ ፈተናዎችን ያለፈና በሁኔታዎቸ መለዋወጥ የማይቀያየር መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገልጸዋል።

ቻይና የምትከተለውን ወጥና በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት እንዲሁም የዜጎችን ህይወት የሚለውጥ ድጋፍ የማድረግ ፖሊሲን እንደሚያደንቁ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ላለት ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ የጠቀሱት ዶክተር ወርቅነህ  ያላቸውን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ የትብብር አጋርነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በመንግስት የሚተዳደሩ ኩባንያዎችን በከፊል ወይም በሙሉ ወደግል ለማዞር መወሰኗን ገልጸው በዚህም የቻይና መንግስትና የግል ካምፓኒዎች ቢሳተፉ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነትና ተጠቃሚነት እንደሚያጠናክር እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና አፍርካ ፎረም ፕሬዝዳንት ሺ በአፍሪካ ለሚደረግ ኢንቨስትመንት ይፋ ያደረጉትን የ60 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፋይናንስ ድጋፍ ያደነቁት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ለመወጣት ትሰራለችም ብለዋል። 

የቻይና የውጭ ጉይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት አድንቀው ኢትዮጵያ እምነት የሚጣልበት አጋር በመሆኗ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ለውጥ ምክንያት በቻይና በኩል የሚደረግ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ እንደለለ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ሚስተር ዋንግ ግንኙነቱ ሁሉን አቀፍ፣ ታሪካዊና የማይናወጥ ነው በማለት ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ዋንግ ይ ጠቅላይ ሚነስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በቻይና በሚካሄደው ሁለተኛው የ ‘የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ’ የመሪዎች ስብሰባ አገራቸውንና አፍሪካን በመወከል እንዲገኙ በፕሬዚዳንት ሺ መጋበዛቸውን ገልጸው፣ ይህም ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ልዩ ቦታ የሳያል ብለዋል። (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)