ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመንገዶች ባለስልጣንና ጠቅላይ አቃቤ ህግን ጎበኙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤቶችን ጎበኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንገዶች ባለስልጣን በ100 ቀናት የስራ እንቅስቃሴን  ለውጥ ተመልክተዋል።

ባምቢስ አካባቢ በሚገኘው የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት በመገኘትም በቢሮው የተደረገውን የለውጥ ሂደት ቃኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጉብኝቱ ዓላማ “የተጀመረው ለውጥ መሬት ላይ ማረፉን ለመመልከት ነው”  ብለዋል።

ሁለቱም ተቋማት ለለውጥ ሂደት ወሳኝ ሚና አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በጉብኝቱ ጥሩ ነገሮችን ተመልክተናል” ሲሉም ገልጸዋል።

በለውጡ ሂደት “ላይነኩ የተቋቋሙ የሚመስሉ ነገሮችን በመለውጥ ህዝብ ጥሩ አገልግሎትና መስተንግዶ ማግኘት የሚችልበት አጋጣሚ እየተፈጠረ መምጣቱን አይተናል” ሲሉም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተቋማትን የለውጥ ሂደት አንድም በሪፖርት በሌላ በኩል ደግሞ በአካል በመገኘት እንመለከታለን ብለዋል።

በመሆኑም ተቋማት በ100 ቀናት ያደረጓቸውን መሻሻሎች መጎብኘታቸውን እንደሚቀጥሉ ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝቱ በፌዴራልና በክልል ተቋማትም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ (ኢዜአ)