የህግ የበላይነትን በማስከበር ሰላም ለማረጋገጥ ህዝባዊ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲረጋገጥ የህዝቡ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ ።  

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው በመግለጫ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እና የክልሉ ህዝብ ሰላም ተረጋግጦ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ከፍ እንዲል ለረጅም ዓመታት መራራ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል ብሏል።

መድሎ እና የብሄር ጭቆና፣ በራስ ሀብት በአግባቡ አለመጠቀም እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግርን መነሻ በማድረግ በተደረገ ትግል ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎ የኦሮሞ ህዝብ መብት መረጋገጥ ጀምሯልም ነው ያለው።

በአሁኑ ወቅትም የህዝቡ ተስፋ እየለመለመ መጥቷል ያለው የክልሉ መንግስት፥ ይሁን እንጂ ሥልጣን ከእጃቸው የወጣ አካላት በየስፍራው ሴራ በመሸረብ አሁን የተጀመረው ለውጥ እንዲደናቀፍ  ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን አስታውቋል።

እያወቀም ይሁን ባለማወቅ ትናንት የኦሮሞን ህዝብ ለመስበር ለሚፈልግ አካል መሳሪያ እየሆኑ ያሉ አካላት መጨረሻቸውም ጥፋት እና ችግር እየሆነ ነው ሲልም አስታውቋል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከመንግስት ጋር የደረሰው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩም ትናንት ሊሰብሩን የሚፈልጉ ኃይሎች ፍላጎትን ለማሳካት በሚችል መልኩ የኦሮሚያ ክልል ሰላም እየደፈረሰ መሆኑንም ገልጿል።

በተለይም በአራቱ የወለጋ ዞኖች እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ በየእለቱ የሰው ህይወት እያለፈና ንብረት እየወደመ ነው ያለው የክልሉ መንግስት፥ መንገዶች በመዘጋታቸው የንግድ እንቅስቃሴ በመቆሙ ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጠ ነው ብሏል።

በአንድንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸውም የኦሮሞ ህዝብ ከጨለማ ወደ ብርሃን መውጣት በጀመረበት በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህጻናት መሃይምነት ውስጥ እንዲቆዩ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል።

የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት መሥጠት በማቆማቸው ወላድ እናት በመንገድ ላይ ህይወቷ እያለፈ ነው፣ የውሃና የመንገድ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል፣ የንግድ እንቅስቃሴም በመቆሙ ህዝቡ ለከፍተኛ ችግር ከመጋለጥም አልፎ የፀጥታ ስጋት ውስጥም ገብቷል ብሏል።

አሁን ወቅቱ ሥልጣንን ማዕከል በማድረግ እውነትን እየሸሸጉ እርስ በእርስ ድንጋይ የምንወራወርበት አይደለም ያለው የክልሉ መንግስት፥ ከሁሉም በፊት የህዝቡን ሰላም በማስቀደም ችግሮቻችንን የምንቀርፍበት ነውም ብሏል።

የኦሮሞ ህዝብ ለውጡን ለማስቀጠል በጋራ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ ህዝብ ውስጥ በመንቀሳቀስ አደጋ ማድረስ፣ ለህዝቡ የቆመን የፀጥታ ሀይል መግደል፣ የጦር መሳሪያ በመዝረፍ ሁከት በመፍጠርም ይሁን ሆን ብለው ጉዳቱን እያወቁ፣ እያዩ እና እየሰሙ ኦሮሚያን የጦርነት አውድማ ለማድረግ አቅደው እንደሚሰሩ ሀይሎች “ኦሮሞ ሀገር መምራት አይችልም፥ የሽግግር መንግስት ነው የሚያስፈልገው” ማለት የተጀመረውን ለውጥ ያደናቅፋል አንጂ አያሻግርም ብሏል።

በህዝቡ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ማባባስ እንጂ ሰላም እንደማይሆንም ነው የክልሉ መንግስት ያስታወቀው።

ያለው መፍትሄም ለህዝቡ ነው የምታገለው የሚለው ማንኛውም አካል ለህዝቡ ሰላም ቅድሚያ መስጠት አለበት፤ የህግ የበላይነት ተከብሮ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ወደነበረበት መመለስ እንዳለበት ገልጿል።

ጦርነት አስነስቶ ደም በማፋሰስ መንግስትን ማዳከም እና ማፍረስ ለጠላት መንገድ ይከፍታል እንጂ ለሀገር አንድነት መፍትሄ አይሆንም ብሏል።

ለአንድነት እና ለሰላም ያለው አማራጭ ህግን ማክበር እና ማስከበር ነው፤ ለዚህ ደግሞ መንግስት ግዳጅ ስላለበት የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲሰፍን እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

ለዚህም በሁሉም አካባቢ የሚገኘው ህዝብ ለሰላም መጠናከር  የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጥሪውን አስተላልፏል።