የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድከር ለሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድከር በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አመሻሹን አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን፥ በኢትዮጵያም የሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዮ ቫራድከር በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአየርላንድ መንግስት ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት ለውጦች ከሚደግፉ የአውሮፓ ሃገራት ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኑ ይታወቃል።

ከዚህ ባለፈም አየርላንድ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀጠናው አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን ለምታደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ ስትሰጥ ቆይታለች።

ኢትዮጵያና አየርላንድ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ አየርላንድ ቆንስላዋን በ1986 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ስትከፍት ኢትዮጵያ ደግሞ በ1995 ዓ.ም ደብሊን ላይ ኤምባሲዋን መክፈቷ ይታወሳል።( ምንጭ: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት )