የትግራይ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ ሊረበሽ አይገባም – ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የክልሉ ህዝብ ህጋዊ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ሳይረበሽ በልማቱ ላይ ማተኮር እንደሚገባው አስታወቁ።

ዶክተር ደብረጽዮን ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫውም የመከላከያ ሰራዊት ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ህጋዊና ኃላፊነቱንም ለመወጣት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በመሆኑም የክልሉ ህዝብ ይሄንን ተገንዝቦ ያለምንም መረበሽ የልማት ስራውን በተረጋጋ መልኩ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን ህዝቡ የሚያነሳው የህገ መንግስት ይከበርልን ጥያቄ እራሱ ከማክበር የሚጀምር መሆኑንም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማስከበርን ጉዳይም ህዝቡ በፈጠረው አደረጃጀት አንድነቱን ማስቀጠል እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ባደረጉት የጋራ ስምምነት የሁመራ ኦምሃጀር መንገድ መከፈትም ለሁለቱ ህዝቦች ግንኙነት ጠቃሚ እንደሆነ ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

መንገዱ የሁለቱን ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከማሳደግ ባለፈው ቀጣይ ህጋዊ መስመር ለማስያዝም ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል።(ኢዜአ)