በምዕራብ ጎንደር ዞን በተፈጠረው አለመግባባት የመከላከያ ሀይል የንጹሃንን ህይወት አጥፍቶ ከሆነ ተጣርቶ ተጠያቂ ይሆናል – ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

በምዕራብ ጎንደር ዞን ጭልጋና መተማ ወረዳዎች በተፈጠረው አለመግባባት የመከላከያ ሀይል የንጹሃንን ህይወት አጥፍቶ ከሆነ ተጣርቶ ተጠያቂ እንደሚሆን የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል፡፡

እንደ ጄኔራል ብርሃኑ ገለጻ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ንጹሃንን ዜጎች ላይ ተኩሰው ህይወት አጥፍተው ከሆነ ከተጠያቂነትም ባሻገር ይቅርታ የመጠየቅና ካሳ የመክፈል ተግባራትን ያከናውናል፡፡

የሃገር መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ሰዎችን አይገልም ያሉት ጄኔራሉ ጉዳዩ ተጣርቶ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል፡፡ በችግሩ የተከሰተውን ሁኔታም ከክልሉ ባለስልጣናት፣ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጉዳዩ በጥልቀት እየተጣራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ንጹሃንን ገድለዋል በሚል በህዝቡ ዘንድ የተሰራጨው መረጃም በመጣራት ሂደት ላይ እንደሆነ ገልጸው ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል በምዕራብ ኦሮሚያ ታጥቆና ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ሃይል የመከላከያ ሃይሉ ትጥቅ የማስፈታት ስራ የሰራ ሲሆን በዚህም የአካባቢውን ሰላም መመለስ እንደተቻለም ጄኔራል ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በአካባቢው የክልል እና የወረዳ መዋቅር እንዲፈርስ ያደርጉ የነበሩ የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎችና ሌሎችም አካላት በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነውም ብለዋል፡፡

በሌላም በኩል በትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ የተፈጠረውን አለመግባባት ከህዝቡ ጋር ውይይት በማድረግ መፈታቱን ጄኔራሉ ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ የፖለቲካ ነጋዴዎች በአካባቢው የሃገርን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

መከላከያው ለምን ጦሩን እንደሚያንቀሳቅስ ሪፖርት እንዲደረግለት የሚፈልግ አካል ቢኖርም የማይመለከተው በመሆኑ ሪፖርት አይደረግለትም ሲሉ ጄኔራል ብርሃኑ መግለጫቸውን አጠቃለዋል፡፡