የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ 4ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ከፊታችን ጥር 19 ቀን ጀምሮ በሐዋሣ ከተማ እንደሚካሄድ የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።

ዘንድሮው የሚካሄደው  4ኛ የኢህአዴግ የወጣቶች ሊግ  ጉባኤ ከጥር 19 እስከ ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ተገልጿል ።

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የአዘጋጅ ኮሚቴው ቃል አቀባይ ጫላ ኦሊቃ የጉባኤውን ዝግጅት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፥ ጉባዔው ከእናት ድርጅቱ ጉባኤ ማግስትና ሀገሪቱ በሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ባለችበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑን ተናግሯል።

ጉባኤውን ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅቶች በሙሉ የተጠናቀቁ ሲሆን፥ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች የሊግ ተወካዮችና ተጋባዥ እንግዶችና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

ጉባኤው በ3ኛው መደበኛ ጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን መሠረት  በማድረግና አፈጻጸማቸውን በመገምገም፥ የነበሩ ጥንካሬዎች የሚቀጥሉበትና እጥረቶች የሚታረሙበት አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአባል ሊጎች ደረጃ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን በማጠናከርና በማቀናጀት በሊጉ ውስጥ ዴሞክራሲያዊነትን በሚያሰፋና የሊጉን ተቋማዊ አቅም በሚያጠናክር መልኩ ይካሄዳልም ነው የተባለው።

ሊጉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ በመውጣት በወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም በስብዕና ግንባታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉትን አቅጣጫዎች እንደሚያስቀምጥ ተገልጿል ።(ምንጭ:የኢህአዴግ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት )