የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ያዘጋጀው የእርቀ ሰላም መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ያዘጋጀው የእርቀ ሰላም መድረክ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፥ “ሀገራችንን የምንጠብቀው እኛ ነን፤ የሀገራችን ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም፤ የእኛ ጉዳይ ነው፤ ሁላችንንም ስለ ሀገራችን ሰላም ያገባናል” ብለዋል።

“አባቶቻችን እና ልጆቻችን የከፈሉትን መሰዋእትነት ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ከዚህ በፊት ያሳለፍናቸውን ክፉ ጊዜዎች በማሰብ ሰላምን በማስፈን ህዝቡን ማሳረፍ አለበን” ሲሉም ተናግረዋል።

“ሰላም ከሁሉም ነገር ቀዳሚው ነው፤ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገሪቱን ሰላም ማምጣት አለባቸው” በማለት ከታላቅ አደራ ጋር ጭምር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ጦርነት አንፈልግም፤ ህዝባችን በሰላም ወጥቶ መግባት ይፈልጋል” ያሉት አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እርስ በእርስ መጋጨት ትተው ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲቄዎች በአንድነት በመቆም በፓርቲዎቹ መካከል እርቅ እንዲሰፍን የጠየቁ ሲሆን፥ “ፓርቲዎቹ የቀረበላቸውን ጥያቄ እስኪቀበሉ ድረስ አንቀመጥም ወደ ቤትም አንሄድም” ሲሉ ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹም በአንድነት በመሆን ከኦሮሞ አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲቄዎች የቀረበላቸውን የሰላም እና የእርቅ ስምምነት መቀበላቸውን አስታውቀዋል።

የኦሮሞ አባ ገዳዎች በመድረኩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሰረትም ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማእከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ በመድረኩ፥ የገዳ ስርዓት በቀልን ሳይሆን መዋደድን፣ አንድነትን እና መቀራረብን ነው ያስተማረን ሲሉ ተናግረዋል።

የአንድ ሀገር እና የአንድ አባት ልጆች በፖለቲካ ምክንያት መገዳደል እና አንዱ አንዱን ከሀገር ማባረር መቅረት አለበት ሲሉም ዶክተር አለሙ ገልፀዋል።

እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገባነውን ቃል መጠበቅ አለብን ያሉት ዶክተር አለሙ፥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በኤርትራ የተደረሰውን ስምምነት ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ እንፈልጋለንም ብለዋል።

ዶክተር አለሙ ስሜ አክለውም፥ ከዚህ በኋላ አንዱ አንዱን ማዳከም እና ጦርነት አያስፈልግም ብለዋል።

በኦዲፒ በኩል እስካሁን ስለሰላም ከመስራት ወደኋላ አልተባለም፤ ከአባገዳዎች እና ከሌሎች የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየሰራ ነው፤ ሆኖም ግን ይህ እየተሰራ እያለ የሰዎች ህይወት እያለፈ ነው፤ ባንኮች እየተዘረፉ ነው፤ ይህ ሲሆን እኛም ህግ ለማስከበር ተገደድን ሲሉም ተናግረዋል።

መንግስት ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር በተለየ የደረሰው ስምምነት የለም፤ ሆኖም ግን የሚጠበቅበትን ሳያደርግ ቀርቷል፤ ያጎደለው ነገር አለ የሚባል ከሆነ ደግሞ በግልጽ ይጠየቅ ብለዋል።