ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ እየተሳተፉ ነው።

የተለያዩ ሃገራት እና ቢዝነስ መሪዎች የሚሳተፉበት የ2019 የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዛሬ በይፋ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓለም ሃገራት መሪዎች በተገኙበት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በንግግራቸውም በኢትዮጵያ ባለፉት 10 ወራት ስለተደረጉ ማሻሻያዎችና ለውጦች ያነሳሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

የተለያዩ ሃገራት እና ቢዝነስ መሪዎች በስዊዘርላንዷ ዳቮስ ከተማ በየአመቱ በመገናኘት በወደፊቱ የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።

በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ከአለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን የዱባይ ኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሀመድ አል ሼይባን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅትም የኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ በመስተንግዶና በእርሻ ቢዝነስ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት ያለው መሆኑን ገልጿል።

እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት ከተውጣጡ የኩባንያ የስራ ሃላፊዎች ጋር የግል ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚቻልባችው ዕድሎችን ለመለየት የሚያስችል የኢንቨስትመንት ስትራቴጂክ ውይይት አካሂደዋል።

ይህ ጠንካራ ውይይት በኢትዮጵያ ያለውን ያልተነካና እምቅ የኢንቨስትመንት ሀብትና ፖሊሲ ቅድሚያ ሊሰጥባችው የሚገቡ ነጥቦችን አመላክቷል።

በተጨማሪም ዶክተር ዓብይ በዛሬው ዕለት ከኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን ሃላፊ ጆርጅ ሶሮስ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በሀገሪቱ የተቀናጀ የምርጫ ሥርዓት ማካሄድ በሚቻልበት ዙሪያ፣ በዴሞክራሲ ለውጥ ላይ ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች እና ሁሉን አቀፍ የሆነ የፍትህና የኢኮኖሚ እድገን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።(ኤፍቢሲ)