የአቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ጉዳይ በፍርድ ቤት ይታያል-የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን

አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ)ን በጥረት ኮርፖሬት ከደረሰ የሀብት ብክነት ወንጀል ጋር በተያያዘ ጠርጥሯቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት ፥ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን  አረጋግጠዋል።

ሁለቱ  ግለሰቦች  ጉዳያቸው በክልሉ ፍርድ ቤት እንዲታይ የሚደረገው የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመውም በክልሉ ስለሆነ መሆኑን ኮሚሽነሩ ያስታወቁት።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በግለሰቦቹ ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችለኝን ከበቂ በላይ ማስረጃ መሰብሰቡንም በመግለጫው ተጠቁሟል።

በዚህም የጥረት ኮርፖሬሽን ብክነት ተፈጽሞብኛል ብሎ በሠጠው ጥቆማ መሰረት ከአምስት ኩባንያዎች የአክስዮን ግዢ ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ብልሹ አሠራር ኦዲት  መደረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል ።

በተካሄደው የኦዲት ግኝት መሠረትም ክስ ሊያስመሰርት የሚችል ማስረጃዎች በመገኘታቸው ምክንያት በጉዳዩ ዋነኛ ተሳታፊ ናቸው ተብለው ተጠርጥረው መያዛቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሌሎች ሁለት ኩባንያዎችም የኦዲት ግኝት ላይ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ኮሚሽነሩ አንስተዋል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ጥረት በመሠረታቸው ስድስት ኩባንያዎች ላይ የተለያየ ብልሹ አሠራሮችን መፈጸማቸውን አብራርተዋል።

ስድስቱ ኩባንያዎች ሲመሰረቱም የአዋጭነት ጥናት ያለመካሄዱን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፥ 35 ሚሊየን ብር ለነዚህ ኩባንያዎች ግዢ መውጣቱን ገልጸዋል።

ግዢያቸው ከተፈጸመ በኋላም ወደ ስራ ያልገቡ ሲሆን፥ ጥረትንም ለተጨማሪ ኪሳራ ዳርገውታል ብለዋል።

ጥረት ኮርፖሬሽን በአጋርነት ከሚሰራቸው ኩባንያዎች ጋርም ከኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አሰራርና ህግ ውጪ 7 ሚሊየን ብር ለሁለት ኩባንያዎች መሰጠታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ከባለሙያ ግምት ውጪ አክስዮን መግዛት የተገዛን ኩባንያ መልሶ መሸጥ መታየቱንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሦስት ግለሰቦች ለሚተዳደር አንድ የማዕድን ኩባንያ ላወጣው የ1000 ብር የአክስዮን ዋጋ ጥረት በአንጻሩ 2 ሺህ 200 ብር እንዲገዛ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ግለሰቦቹ የ4 ሚሊየን 320 ሺህ ብር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፥ ጥረትን ለኪሳራ ዳርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም ለካፒታል ዕድገት ለሀገር ውስጥ ገቢ መክፈል የነበረበትን 1 ሚሊየን 296 ሺህ ባለመክፈሉ ጥረትን ባለዕዳ ማድረጉን አብራርተዋል።

ለፋብሪካ ግንባታ የሚውል የ17 ሚሊየን ብር ግብዓት ተገዝቶ እስከአሁን ስራ ላይ ባለመዋሉ ለብልሽት መዳረጉን ጠቅሰዋል።

በመጨረሻም  ከሁለቱ ግለሰቦች  ክስ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሌሎች  ተጠርጣሪዎች የሚኖሩ መሆኑን ኮሚሽነሩ  አስታውቀዋል።