የትግራይ ክልል ምክር ቤት የ6 ወራት የስራ አፈፃፀምን ገመገመ

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የ2011 የ6 ወራት እቅድ እና የስራ አፈፃፀምን ገምግሟል፡፡

የትግራይ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 14 ተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በመቐለ እየተካሄደ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የተሰሩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ምክትል ርስሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ከመሬት፣ ከኢንተርፕራይዞች፣ ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከገበያ ትስስር እና ከመስኖ ልማት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን እና በዘርፎቹ የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም በቀጣይ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ የጤና መድንን በተመለከተ እስከ ጥር ሰላሳ ሰድረስ 80 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ የተለያዩ ስራዎች ቢሰሩም የተሳካው ግን 30 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ስለሆነም በቀሪዎቹ ጊዜ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንዲገባ ነው በሪፖርቱ  የተገለፀው፡፡

ከወጣቶች የስራአጥነት ጋር በተያያዙ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች መሰራቱን የገለፁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በስድስት ወራት ብቻ 50 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች የአጫጭር ስልጠናዎችን ወስደዋል ብለዋል፡፡

የሴቶች እና የወጣቶች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ተሳትፎን ለማጎልበት የፋይናንስ ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የክልሉ መንግስት በ2011 የማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ከኢፈርት እና ከትግራይ እርዳታ ድርጅት ጋር በመተባበር 346 ሺህ በላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖች የእህል እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

ከነዚህም መካከል ከ75 ሺህ በላይ ዜጎች በሃገሪቷ ውስጥ በነበሩት ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው የመጡ መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡

ሌላው በሪፖርቱ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል እንደ ሃገር ጠንቅ እየሆነ ያለውን ሙስና ለመከላከል ሃብት በማስመዝገብ ሙስናን ለመቆጣጠር በሚሰራው ስራ በ2011 3 ሺህ ሰዎች የሃብት መጠናቸው እንዲመዘገብ በእቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን እስካሁንም 2 ሺህ 400 የመንግሥት አመራሮች ሃብታቸው መመዝገቡ ነው የተገለፀው፡፡

በክልሉ ሃብታቸውን ማስመዝገብ የሚገባቸው መንግስት ሹመኞች ትክክለኛ የሃብት በመጠናቸው እንዲመዘገብ ጥናት የተካሄደ ሲሆን በልዩ ሁኔታ የሃብት መጠናቸው እንዲጣራ የተደረጉ እና ወደ ህግ መቅረብ ያለባቸውን አካላትንም ወደ ህግ ለማቅረብ አስፈላጊውን የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በክልሉ በቱሪዝም በስፖርት እና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ባለፉት ስድስት ወራት የታቀዱ እና የተሰሩ ስራዎች ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት ቀርበዋል፡፡

በክልሉ የሚፈፀሙ የመንግስት ስራዎች በጥናት፣ ምርምርና ቴክኖሎጂ ተደግፈው የሚከናወኑ መሆናቸውንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገልጸዋል፡፡