17ኛው የኢትዮጵያ አርብቶአደሮች በዓል በደቡብ ክልል በጂንካ እየተከበረ ነው

17ኛው የኢትዮጵያ አርብቶአደሮች በዓል ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት በጂንካ ከተማ በተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በሰላም ሚኒስቴር፣ በደቡብ ክልል እና በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የጋራ አዘጋጅነት የአርብቶአደሩ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአርብቶ አደሩ ህይወት ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶች ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የአርብቶአደር ልማት የፖሊሲና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች ሰነድ እና አብሮነትና የግጭት አፈታት በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ የሚሉ ጥናቶች ነው ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው፡፡

በፓናል ውይይቱ ከሀገራችን የአርብቶአደር አካባቢዎች ተወክለው የመጡ አርብቶአደሮች እንደ የአካባቢዎቻቸው ነባራዊ ሁኔታ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ተመጣጣኝ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታው ዶክተር ስዩም መስፍን ለጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከፌደራልና ከክልል የተገኙ የበዓሉ ታዳሚዎች ከጂንካ 220 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ዳሰነች አካባቢ የሚገኙ አርብቶ አደሮች እና የኦሞ ወንዝን ተከትሎ የተሠሩ የልማት ስራዎችንም ጎብኝተዋል።

በዓሉም በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን ቀጥሏል፡፡ (ምንጭ፡-የሰላም ሚኒስቴር)