አዲስ የተሾሙት የስምንት ሀገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አቀረቡ

በኢትዮጵያ አዲስ የተሾሙት የስምንት ሀገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አቀረቡ፡፡

የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት የካናዳ አምባሳደር አንቶኒ ቼቭረኤር፣ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ፣ የሴራሊዮኑ አምባሳደር ዶክተር ብሪማ ፓትሪክ ካፑዋ፣ የኢኳቶሪያል ጊኒ ክሪስአንቶስ ኦባማ ኦንዶ ናቸው ናቸው ፡፡

በተ­ጨማሪም የስሎቫክ አምባሳደር ድራሆሚር ስቶስ፣ የሰርቢያ አምባሳደር አሌክሳንደር ሪስ ቲች፣ የኮሎምቢያ አምባሳደር ኤልዛቤት ኢንስ ቴይለር ጃይ እና የማልታ አምባሳደር ሮናልድ ሚካሌፍ መሆናቸውን የፕሬዝዳንት ጽኅፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በብሄራዊ ቤተ መንግስት በተካሄደው ስነ-ሥርአት ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢትዮጵያ ከየሃገራቱ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማዳበር ፍላጎት እንዳላትና በተለይም ደግሞ በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ጠንካራ መሰረት እንዲይዝ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አዳዲስ ተሿሚ አምባሳደሮችም በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቷ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ለውጥ በተመለከተ ለአምባሳደሮቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ተሿሚ አምባሳደሮችም በበኩላቸው በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ በየሀገሮቻቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የለውጥ ጉዞ ያደነቁት አምባሳደሮቹ በቀጠናው እንዲሁም በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን እንቅስቃሴም በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ (ምንጭ፡-የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት)