የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አገራዊ ለውጡ ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው የለውጥ ሂደት ላይ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ ።                             

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን ከጥር19 እስከ 21 ድረስ በአዋሳ ከተማ ለማካሄድ ዝግጅቱን  ማጠናቀቁንም በዛሬው ዕለት በሠጠው መግለጫ አመልክቷል ፡፡

በ2000 ዓም ላይ የተመሠረተው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን “ በተጠናከረ የወጣቶች ትግል የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ወደ ፊት ” በሚል መሪቃል በሐዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ገልጿል፡፡

የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሊቀ መንበር ሙቀት ታረቀኝ እንደገለጸው ሊጉ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በወጣቶች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ዙሪያ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሶ ጉባኤው  በአራት አጀንዳዎችን መክሮ የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያቀምጥበት መሆኑን አንስቷል፡፡

ዘንድሮ የሚደረገው የ4ኛው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ ባለችበት ወቅት መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ያነሳው ሊቀመንበሩ ምክንያታዊ የሆነ ወጣትን ለመፍጠር ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋነኛ የትግል አላማ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኢህአዴግ ሊግ ራሱን በማጥራት ሂደት ባደረገው የውስጥ ትግልም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አባላቱን  ከአባልንት ማሰናበቱን ወጣት ሙቀት በመግለጫው አንስቷል፡፡

ከጥር 19 እስከ 21 ድረስ በሚቆየው የኢህአዴግ ጉባኤ 500 አባላት በድምጽ የሚሳተፉ ሲሆኑ 200 ወጣቶች በተጋባዥነት ይሳተፋሉ፡፡

በ4ኛው የኢህአዴግ ሊግ በአጠቃላይ ከ1ሺህ100 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት በመግለጫው  ተመልክቷል ፡፡