የአስተዳደሩ የአገልግሎት አሠጣጥ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አዲስ የተቋማት አደረጃጀት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አዲስ የተቋማት አደረጃጀት እየተሠራ ነው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የአስፈፃሚ ተቋማት ቁጥርን ከ110 ወደ 63 ዝቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህም በሚና መደራረብ ምክንያት ለተዋሃዱ ተቋማት፣ ለታጠፉ ተቋማት እና እንደ አዲስ ለተቋቋሙ ተቋማት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አዲስ አወቃቀር እየተሰራ እንደሚገኝ የከንቲባው ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በከተማ አስተዳደሩ ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃይል ልማት ቢሮ የተዘጋጀ አዲስ አወቃቀር ተግባራዊ በሚደረግበት ሁኔታ ላይ እየመከሩ ካሉ ባለሞያዎች ጋር በመወያየት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ከባለሙያዎች ጋር በነበራቸው ቆይታቸውም አዲሱ የከተማ አስተዳደሩ አወቃቀር መሠረታዊ የአደረጃጀት መርሆችን በተከተለ መልኩ የህዝብ ገንዘብን ለከፍተኛ ብክነት ሲዳርጉ የነበሩ አስፈፃሚ ተቋማት በአዲስ አወቃቀር ለህዝብ ምቹ በሆነ መንገድ እንደሚደራጁ ገልፀዋል፡፡

በአዲሱ አወቃቀር በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ላሉ ተቋማት እና አመራሮች ይመደብ የነበረውን ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት በመቀነስ ገንዘቡ በከተማው ውስጥ ላሉ የልማት ስራዎች እንዲውል እንደሚደረግ እና ተቋማቱ ለከተማው ነዋሪ የሚሰጡትን አገልግሎት ዘመናዊና ምቹ በማድረግ ረገድ አዲሱ አወቃቀር የማይተካ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)