ፍርድ ቤቱ በአቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ የጠየቀውን የቀዳሚ ምርመራ ጊዜ ፈቀደ

ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ በቀድሞው ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁን ላይ የጠየቀውን የቀዳሚ ምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሙስና የተጠረጠሩትን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁንን መመዝገብ ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ በትናንትናው ዕለት መርማሪ ፖሊስ እስካሁን ያከናወናቸውን የምርመራ ውጤቶችና ቀሪ ስራዎችን አድምጧል።

በዛሬው ዕለትም መርማሪ ፖሊስ ለቀዳማዊ ምርመራ የጠየቀውን የ14 ቀናት የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ አግባብነት ተመልከቷል።

መርማሪ ፖሊስ የተጎጂዎችን የህክምና ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ ተጨማሪ የምስክር ቃል ለመቀበልና ተጠርጣሪው ኢ-ሰብዓዊ የመብት ጥሰት እንዲፈፀም አድርገውባቸዋል የተባሉ ስውር እስር ቤቶችን በተጎጂዎች ለማስለየት የተጨማሪ የምርመራ ጊዜው አስፈላጊ ስለመሆኑ አስረድቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው ያለአግባብ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ሃብት ያካበቱ በመሆናቸውና ከተጠረጠሩባቸው ድርጊቶች ውስብስብነት አንፃር ተጨማሪ የምርመራ  ጊዜ ይፈቀድልኝ ሲል ችሎቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በዋስ ቢፈቱ መረጃዎችን ሊያሸሹ፣ እራሳቸውም ሊሰወሩ ስለሚችሉም የዋስ መብታቸው እንዳይፈቀድ ሲል ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ ከህዳር 26 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ እስካሁን በርካታ ምስክሮችን አሰምቷል፤ አሁን ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ አግባብነት የለውም ሲሉ ተቃውመዋል።

መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው የቀዳማዊ የተጨማሪ ጊዜ የምርመራ ስራው ስለመጠናቀቁ ማሳያ ነው ሲሉ ለችሉቱ አስረድተዋል።

የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ በመርማሪ ፖሊስና የተጠርጣሪ ጠበቆች አቤቱታዎችን ከግምት በማስገባት ለማርማሪ ፖሊስ 12 ቀናት የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በተማሳሳይ መልኩ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በእነ ጎሃ አጽብሃ መዝገብ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 16 የቀረቡ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ተመልክቷል።

መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በመመልክት የ12 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ መስጠቱም ነው የተገለጸው።(ኤፍቢሲ)