5ኛው የኢትዮ-ጂቡቲ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በጅቡቲ ሊካሄድ ነው

15ኛው የኢትዮ-ጂቡቲ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በጅቢቲ ሊካሄድ ነው ።

ከኢትዮጵያ 10 የሚደርሱ ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት 15ኛው የኢትዮ-ጂቡቲ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ከፊታችን እሁድ ጥር 19 ጀምሮ እስከ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በጂቡቲ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ከመጪው ሰኞ ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ቀናት ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ተጠቁሟል ።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ ዘርፈ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሲሆኑ፤ በተለይ የጂቡቲ ወደብ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ዋነኛ የወጪና የገቢ ንግድ መስመር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

አገሮቹ በመሰረተ ልማት ከመተሳሰራቸውም ባሻገር የጋራ ኮሚሽን አዋቅረው ግንኙነታቸውን በየጊዜው እየገመገሙ ይገኛሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንደገለፁት፤ ሁለቱ አገሮች የጋራ ኮሚሽን በማቋቋማቸው በትብብር ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት አስችሏቸዋል።

የትራንስፖርት፣ የወደብ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የጉምሩክና የንግድ ጉዳዮች የጋራ ኮሚሽኑ በዋነኝነት የሚያተኩርባቸው የውይይት አጀንዳዎች መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

የጋራ ኮሚሽኑ በእነዚህ ዘርፎች የሁለቱ አገሮች የትብብር ግንኙነት እንዲጠናከር ከመምከር ባሻገር ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በኩል አስር ሚኒስትሮች በስብሰባው ላይ እንደሚሳተፉ የጠቆሙት አቶ ነብያት በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረገውን ስብሰባ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንደሚመራም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ወደ ተለያዩ አገሮች የሚላኩ አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ከመጪው ሰኞ ጥር 20 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለ15 ቀናት ስልጠና እንደሚሰጣቸው ቃል አቀባዩ አመልክተዋል።

ስልጠናው የሚሰጠው በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ኢንስትቲዩት መሆኑን አቶ ነብያት ጠቁመዋል።

ስልጠናው ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ስለሚኖራት ግንኙነት ማሳወቅና አምባሳደሮቹ ስራቸውን በምን አግባብ ማከናወን እንዳለባቸው አቅጣጫ በሚጠቁም ላይ እንደሚያተኩርም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ለሚሰሩ አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶች ስለ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ገለጻ ማድረጋቸው ይታወሳል።(ኢዜአ)