ድሬዳዋ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እየተመለሰች መሆኗ ተገለጸ

ድሬዳዋ ከተማ ወደ መረጋጋት እየተመለሰች በመሆኑ መደበኛ የስራ እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት መመለሱን የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በመከላከያ ሰራዊት፣ በሌሎች የጸጥታ ኃይሎችና በህዝቡ ጥረት እየመጣ ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ የምስራቅ ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ወስዶ እየሰራ ይገኛል።

የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ሳጅን ባንተአለም ግርማ እንደገለጹት ባለፉት አራት ቀናት ወጣቶች ሲያካሄዱት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍና እሱን ተከትሎ የተከሰተው አለመረጋጋት ትላንትና ቆሟል፡፡

ግርግሩን ተከትሎ በመንግስታዊና በግለሰብ ተቋማት ላይ መጠነኛ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ኃላፊው በችግሩ መፈጠርና መባባስ የተጠረጠሩ ቀደም ሲል የተያዙትን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ለተፈጠረው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ወጣቱ ላሳየው ተሳትፎ ዋና ሳጅን ባንተአለም በኮሚሽኑ ስም አመስግነው በወጣቱ ጥያቄዎች ሰበብ ድብቅ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ እስቂያስ ታፈሰ በበኩላቸው የምስራቅ ዕዝ መከላከያ ሠራዊት በከተማው ሰላምን የመጠበቅና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ኃላፊነትን በበላይነት ተረክቦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በተፈጠረው መረጋጋት መደበኛ እንቅስቃሴ በከተማው እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው በቀጣይ የወጣቶቹን መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚደረጉ ተናግረዋል፡፡

በከተማው ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩ ቢረጋገጥም ትላንት በመልካ ጀብዱ ቀበሌ መጠነኛ ግጭት መታየቱን የቀበሌው ነዋሪዎች ገልፀዋል። (ኢዜአ)