የትግራይ ህዝብ ዋነኛ አጀንዳ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት መሆኑን የክልሉ መንግስት ገለፀ

ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ የትግራይ ህዝብ ዋነኛ አጀንዳ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት መሆኑን የትግራይ ክልል መንግስት ገለፀ።

የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ህዝብና መንግስት የጦርነትን አስከፊነት ስለሚረዱ፣ ዋነኛ አጀንዳቸው የሆነው ሰላምን ማስፈን፣ ዲሞክራሲ ማስፋትና መልካም አስተዳደር ማንገስ እንዲሁም ፈጣንና ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ለማረጋገጥ በመታተር ላይ መሆናቸውን አንስቷል።

የትግራይ ህዝብና መንግስት በ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ወቅት፣ ወታደራዊ ፋሽስት ደርግን ለመደምሰስ በተደረገው መራራ ትግል፣ የአማራ ህዝብ፣ ከወንድሙ የትግራይ ህዝብ ጎን ተሰልፎ ተገቢው መስዋእትነት መክፈሉን አስታውሷል።

በመሆኑም የትግራይ ህዝብና መንግስት የታገሉለትን ህዝባዊ መስመር አንግበዉ ወደፊት ከመገስገስ ውጪ በወንድም የአማራ ህዝብ ላይ አፈሙዝ የሚያዞርበት አንዳች ምክንያት የለም ነው ያለው።

በመሆኑም የትግራይ ህዝብና መንግስት ባለፉት ዓመታት፣ በተለያዩ ችግሮች የባከኑባቸውን ጊዜያት ለማካካስ እና የዴሞክራሲና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን ለማሳካት በመሯሯጥ ላይ ናቸው ብሏል::

የክልሉ ህዝብና መንግስት በተያያዙት የበጋ ወቅትም ቢሆን አፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት በማሳለጥ ለ2011/2012 የክረምት ስራ ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን መግለጫው አንስቷል።

ስለሆነም ትላንትም ሆነ ዛሬ የትግራይ ህዝብና መንግስት ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው ያለው መግለጫው፥ አሁንም ቢሆን ጦርነታቸዉ ከድህነት ጋር በመሆኑ ማንኛውም ሰላም ወዳድ ዜጋ ስጋት ሊገባዉ አይገባም ብሏል።

በአጭሩ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዋነኝነት የአማራና የትግራይ ህዝቦች ሰላም ተረጋግጦ የልማት ተቋዳሽ የሚሆኑት፣ በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ተከብሮ፣ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ፣ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ተጠናክሮ ሲቀጥል መሆኑን አስታውቋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)